የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በ2015 ዓ.ም በተካሄደው ከተማ አቀፍ የባዶ ቦታ ልየታና ኦዲት ወቅት ያላግባብ ወደ መሬት ባንክ ገብተዋል ተብለው ቅሬታ የቀረበባቸውን ይዞታዎች መርምሮ ምላሽ የሚሰጥ አሰራር መዘርጋቱን አስታወቀ።
በወቅቱ በተካሄደው ዘመቻ 3 ሺህ 744 ሄክታር (10 ሺህ 097 ፕሎት) መሬት ከህገ-ወጦች ተመልሶ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን፣ ስራው በዘመቻ በመከናወኑ ምክንያት ከ250 በላይ ቅሬታዎች መቅረባቸው ተገልጿል።
የመሬት ባንክና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ክብሮም አሰፋ እንደገለጹት፣ የቀረቡትን ቅሬታዎች እንደየይዞታው ሁኔታ አጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ኮሚቴ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተቋቁሟል።
የመሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፌኑስ ገላና በበኩላቸው፣ የህዝብና የመንግስት መሬት ከወረራ በሚጠበቅበት ሂደት የህጋዊ ባለቤቶች መብት እንዲከበርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የማስተካከያ ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል።
መስከረም 18/2019 ዓ.ም
