ወደ አዲስ አበባ የሚላኩ የሪፈር ታካሚዎችን ቁጥር 95 በመቶ መቀነስ መቻሉን የድሬዳዋ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተቀናጀ አሰራር ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሰኢድ አብዲ አስታዉቀዋል።

የሰው ኃይልና የህክምና ግብአቶችን የማሟላት ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።

በተለይም እናቶች በቤት ውስጥ የሚወልዱበትን ልማድ ለመቀነስ፤ ከከተማው ሩቅ በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ቀርበው እንዲወልዱ የሚያስችል ‹‹የወሊድ ማቆያ›› አገልግሎት በስፋት እየተሰጠ ይገኛል ነዉ ያሉት።

ይህም በቤት ውስጥ ወሊድ ምክንያት የሚከሰቱ የደም መፍሰስና ሌሎች የጤና እክሎችን ለመከላከል መቻሉ ተነግሯል።

ከደም ባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘም ድሬዳዋ ለምስራቅ ሀረርጌና ሶማሌ ክልል ጭምር የደም አቅርቦት እያደረገች መሆኗ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል በዘርፉ የታዩ ተግዳሮቶች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊዉ፤ የህክምና ማሽኖች ብልሽት ሲያጋጥም የሚጠገንበት ከፍተኛ ዋጋ እና መለዋወጫዎች እጥረት ዋናው ፈተና መሆኑን አንስተዋል።

በተለይ የሲቲ ስካን ማሽን ብልሽት ለመጠገን በሚጠይቀው ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱ ለአብነት ተነስቷል።

በግል እና በመንግስት የጤና ተቋማት መካከል በተፈጠረ ቅንጅት፤አቅም የሌላቸው ወገኖች በነጻ እንዲታከሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዉ፤በቀጣይም ዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት የጤና አገልግሎቱን ጥራት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ሊዲያ ደሳለኝ

መስከረም 19/2019 ዓ.

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *