የኢትዮጵያ አየር መንገድ አህጉራዊ የበላይነቱን የሚያጎላ አዲስ ስምምነት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ፈፀመ

አየር መንገዱ አስር እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የቦይንግ የጭነት አውሮፕላኖችን ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል።
 
በስምምነቱ መሠረት አየር መንገዱ ስምንት እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የቦይንግ 777-8 እንዲሁም ሁለት የቦይንግ 777 ኤፍ የጭነት አውሮፕላኖችን የራሱ ያደርጋል።
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ እነዚህን አውሮፕላኖች እ.ኤ.አ ከ2033 እስከ 2035 ባሉት ዓመታት ውስጥ ተረክቦ ሥራ ላይ ያውላቸዋል።
 
ከዚህ በተጨማሪም በቅርብ ዓመታት (ማለትም በ2027 እና 2028) ሁለት ተጨማሪ አዲስ የቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖችን እንዲሁም ከተሳፋሪነት ወደ ጭነት የተለወጡ አራት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እንደሚረከብ አቶ መስፍን አበስረዋል፤ ይህም የአየር መንገዱን የካርጎ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል ተብሏል።
 
የቦይንግ ኩባንያ የንግድ ሽያጭና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊውን የቦይንግ 777-8 የካርጎ አውሮፕላን በማዘዝ በአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ በመሆኑ ትልቅ ዕውቅና የሚሰጠው ውሳኔ ነው ብለዋል።
 
በአሁኑ ወቅት የአየር መንገዱ የካርጎ አገልግሎት ከአጠቃላይ ገቢው 23 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን፣ ይህ አዲስ ስምምነት ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን የ897 ሺህ ሜትሪክ ቶን የጭነት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ የአየር መንገዱን የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የበለጠ የሚያጠናክር ይሆናል።

የውልሰው ገዝሙ
 
መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *