የማቲዎስ ወንዱ የሕፃናት ካንሰር ፋውንዴሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዱ በቀለ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ትላንት መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የ72 አመቱ አቶ ወንዱ፣ በካንሰር ሕመም ያጡትን የልጃቸውን የማቲዎስን ስም በመሰየም እ.ኤ.አ. በ2004 ፋውንዴሽኑን ከመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ፣ ይከፈላቸው ከነበረው የመንግሥት የኃላፊነት ቦታ በፈቃደኝነት በመልቀቅ ሕይወታቸውን ሙሉ ለበጎ አድራጎት ሥራ ሰጥተዋል።
ፋውንዴሽኑ ላለፉት 22 ዓመታት ከ5,000 በላይ ለሚሆኑ የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና፣ የትራንስፖርት፣ የምግብና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ የካንሰር እና የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች እንዲወጡ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘጠኝ ያህል ታላላቅ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን 10 ፕሮጀክቶችን ዘርግቶ እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው። ከሚሠራባቸው ፕሮጀክቶች መካከልም የልጆች ጤና፣ ትምባሆ፣ እንዲሁም የሳንባ ካንሰርን የሚመለከቱት ይገኙበታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ያልተወሰነው ይህ ተቋም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሙከ ጡሪ እና በአማራ ክልል አዲስ ዘመን በሚገኙ ሆስፒታሎች የጀመረው ሥራ ውጤታማ ሆኖ የጤና ሚኒስቴርን ትኩረት በመሳቡ በ150 ሆስፒታሎች ውስጥ ለማስፋፋት መታቀዱን አቶ ወንዱ ከዚህ ቀደም ከጣቢችን ጋር በነበራቸው ቁይታ ገልጸውልን ነበር። ይህ ብቻም አይደለም፤ ከጤና ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎች እንዲወጡም የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
የሳንባ ካንሰር ፕሮጀክቱም ለሌሎች የካንሰር ሕመሞች በ36 ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና እንዲሰጥ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑንም ነግረውናል።
በነገራችን ላይ የማቲዎስ ወንዱ ፋውንዴሽን አነሣሥ የካንሰር ታማሚዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችንም በሚመለከት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
አቶ ወንዱ በቀለ በቅርቡ በኮላንጂዮካርሲኖማ (የሐሞት ቧንቧ ካንሰር) ሕመም ታመው በሕክምና ላይ ነበሩ።
የአቶ ወንዱ በቀለ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 6:00 ሰዓት ይፈጸማል።
ኤትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለፋውንዴሽኑ የሥራ ባልደረቦች መጽናናትን ይመኛል።
መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም
የአቶ ወንዱ በቀለ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ሰኞ ይፈጸማል
