የእንቦጭ አረም ከጣና ሃይቅ አልፎ በአባይ ወንዝ ላይ ስጋት መደቀኑ ተነገረ

የጣና ሃይቅና ሌሎች የዉሃ ልማት ኤጀንሲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ የጣና ሃይቅ ብቻም ሳይሆን የአባይ ወንዝ በእንቦጭ ተወሯል ፤መንግስት ግን አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ አይደለም ብሏል፡፡

በኤጀንሲዉ የብዝሃ ህይዎት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘዉ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤ የእንቦጭ አረም ከጣና ሃይቅ አልፎ በአባይ ወንዝ ላይ እየተስፋፋ ነዉ ብለዋል፡፡

የጣና ሃይቅ በእንቦጭ አረም ከመወረሩ ባለፈም በዚህ አመት በከፍተኛ ሁኔታ ዉሃዉ እየቀነሰ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲዉ የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ እንዲያደርጉ ቢጠይቅም ከባለፉት ሁለት አመታት ወዲህ የተገኘ ድጋፍ እንደሌለም አስታውቋል፡፡

አብዛኛዉን ጊዜ አረሙን የማስወገድ ሥራዉ በሰዉ ሃይል እንደሚሰራና አሁን ላይ ግን በህብረተሰቡ ዘንድ የመሰላቸት ሁኔታ ታይቶበታል፡፡

በመሆኑም መንግስት ጣናን ብቻም ሳይሆን የህዳሴ ግድብን ለመታደግ በሚሰራዉ ስራ ላይ ትኩረት ቢያደርግ ሲሉም አቶ መዝገቡ ጠይቀዋል፡፡

ጣና ሃይቅ በእንቦጭ አረም ተወሮ ክፉኛ ከታመመ እነሆ 11 አመታት ተቆጥረዋል፡፡
በሃይቁ ላይ የተከሰተዉን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የማስታገሻ ስራዎች ቢሰሩም ሃይቁን ግን ከህመሙ የሚፈዉስ መድሃኒት እስካሁን አልተገኘም፡፡

ይህ አረም ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ደግሞ ከሃይቁ አልፎ በአባይ ወንዝ ላይ እየተስፋፋ መምጣቱን ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

በዲያስፖራዉ ማህበረሰብ በጣና ትረስት ፈንድ ይደረግ የነበረዉ የአይነት ድጋፍ እንደተቋረጠም ተነስቷል፡፡
በበጀት እጥረት ምክንያትም ሶስት ማሽኖች ስራቸዉን አቁመዋል ነዉ የተባለዉ፡፡

በጉዳዩ ላይ የዉሓና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፤ለሃይቆቻችን ስጋት የሆነዉን የእንቦጭ አረምን ችግር ለመፍታት በተፋሰስ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

በአባቱ መረቀ

ሰኔ 09 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *