የነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ የጉድለት መጠን እስከ ሰኔ 30/2016 ድረስ ከ68 ቢሊየን ብር በላይ ማለፉን ባለስልጣኑ ለጣቢያችን ገልጿል።
የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከግንቦት ወር 2015 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2016 ድረስ ከ68ቢሊየን 3መቶ42 ሚሊየን ብር በላይ የዕዳ መጠን መመዝገቡን ነው የነገሩን።
በሌላ በኩል ባለስልጣኑ ባለፉት 12 ወራት እስከ ሰኔ 28 /2016 ድረስ ከ29 ቢሊየን ብር በላይ የነዳጅ ድጎማ ማድረጉንም ገልጸዋል።
እስከ ሰኔ 28/2016 ባለው ጊዜ ውስጥም ለ1መቶ 99 ሺህ 5መቶ 10 ተሽከርካሪዎች ድጎማው መደረጉንም ነው ያነሱት።
ከዚህ በተጨማሪ ከ3ሚሊየን 6መቶ ሺህ ሊትር በላይ ናፍጣ ወደ ማደያዎች ለማሰራጨት ታቅዶ ከ1ሚሊየን 1 መቶ ሺህ 52 ሊትር በላይ ናፍጣ ማሰራጨት መቻሉን ነው የገለጹት።
ከ2 ሚሊየን 2መቶ ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ለማደያዎች ለማሰራጨት በእቅድ ተይዞ እንደነበር ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ከ8መቶ 22ሺህ ሊትር በላይ መሰራጨቱን ነግረውናል።
ባለስልጣኑ ለዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት እንደምክንያት ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ሲስተሙ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ስርዓት በመላው አገሪቱ በስፋት አለመተግበሩ እንዲሁም በጅቡቲ የነዳጅ ጭነት መረጃ በአግባቡ አለመግባት የሚሉት ይገኙበታል።
በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም
