የኩላሊት ካንሰር /Renal Cell Carciroma/

በ2020 በዓለማችን ላይ 4መቶ31ሺህ 2መቶ88 ሰዎች በኩላሊት ካንሰር ተጠቅተዉ የነበር ሲሆን 1መቶ 80ሺህ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸዉ አልፏል፡፡
የኩላሊት ካንሰር በዓለም ላይ ከሚከሰተዉ ከጠቅላላዉ የካንሰር ህመም ዉስጥም 2.4 በመቶዉን ድርሻ ይይዛል፡፡

በአዋቂዎች እንዲሁም በህፃናት ላይ ሊከሰት የሚችል የካንሰር አይነት ነው።
ታዲያ በጉዳዩ ላይ በቅዱስ ጳዉሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የዩሮሎጂ ሃኪም፣ አሲስታትንት ፕሮፌሰር እና የትምህርት ክፍሉ ሀላፊ ከሆኑት ከዶክተር ማስረሻ ሰለሞን ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

የኩላሊት ካንሰር በምን ይከሰታል?

እንደ ሌሎች ህመሞች ይህ ነዉ የሚባል ምክንያት በአብዛኛዉ የለዉም፡፡
ነገርግን እንደ አጋላጭ የሚነሱ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በዘር፣ ከፍተኛ ዉፍረት መኖር እንዲሁም ሲጋራ ማጬስ እንደ አጋላጭ ምክንያት ይነሳሉ፡፡
ይህ ማለት ግን ከፍተኛ ዉፍረት ያለበት እንዲሁም ሲጋራ የሚያጬስ ሰዉ ሁሉ ለኩላሊት ካንሰር የተጋለጠ ነዉ ማለት አይደለም፡፡

ምልክቶቹስ ምን ይመስላሉ?

የኩላሊት ካንሰር ብዙ ጊዜ ምልክት አያሳይም፡፡
ብዙ ጊዜ የሚገኙትም ለሌሎች ህመሞች ምርመራ ሲደረግ በአጋጣሚ ነዉ፡፡
ምልክት ካሳየ ግን በዋነኝነት ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች ሶስት ዓይነት ናቸዉ፡፡
የመጀመሪያዉ የጎን ህመም ነዉ፡፡ ኩላሊቱ በታመመበት ጎን በኩል ከባድ የጎን ህመም ይኖራል፡፡
ሁለተኛዉ ደም የቀላቀለ ሽንት ይኖራል፡፡

ሶስተኛዉ ደግሞ በኩላሊታችን በኩል በእጅ የሚነካ እብጠት መኖር ናቸዉ፡፡
ጉዳዩን ዉስብስብ የሚያደርገዉ ደግሞ ሶስቱንም በአንድ ቦታ አለማግኘቱ ነዉ፡፡ 10 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸዉ ሶስቱንም ምልክቶች ሊያሳዩ የሚችሉት፡፡

ካንሰሩ መታከም ካልቻለ ሊያደርስ የሚችለዉ የጎንዮሽ ጉዳት?

ካንሰሩ በፍጥነት ከተስፋፋ ወደ ሌሎች የሰዉነት ክፍሎች ሊዛመት ይችላል፡፡
ከእዚህ ዉስጥም ወደ ሳምባ፣ አጥንቶች እንዲሁም ወደ ጡት ሊዛመት ይችላል፡፡
ስለዚህ ዕጢዉ ቶሎ ካልታከመ እንዲሁም በፍጥነት የሚዛመት ዓይነት ባህሪይ ካለዉ ሌሎች የሰዉነት ክፍሎችን የማጥቃት ዕድሉ ከፍተኛ ነዉ፡፡

ህክምናዉ ምን ይመስላል?

ሁሉም የኩላሊት ካንሰር አይነቶች ማለት በሚቻል መልኩ ለኬሞቴራፒ እንዲሁም ለራዲዮቴራፒ ምላሽ የሚሰጡ አይደሉም፡፡
ስለዚህ ቀዶ ህክምና ማድረግ የግድ ይላል፡፡

የቀዶ ህክምና ዓይነቶቹ ደግሞ ብዙ ዓይነት ናቸዉ፡፡ የካንሰር ዕጢዉን ብቻዉን ማዉጣት አልያም ደግሞ ዕጢዉን ከነ ኩላሊቱ ማዉጣት ሌላኛዉ መፍትሄ ነዉ፡፡
ይህ የሚሆነዉ ታዲያ ዕጢዉ ምን ያህል ተስፋፍቷል የሚለዉን በማየት ነዉ ፡፡ ሀኪሞች በሚያዩት ልክ በከፍተኛዉ ከተስፋፋ ከነ ኩላሊቱ ካልሆነ ደግሞ ዕጢዉን ብቻ ማስወገድ ይቻላል፡፡

ሁለቱም ኩላሊቶች በካንሰር ቢጠቁስ ህክምናዉ ምን ሊመስል ይችላል?

ይህ ክስተት ካጋጠመ Nephron-Sparing Surgery በሚባል የቀዶ ህክምና ዓይነት የሚወገድ ይሆናል፡፡
Nephron-Sparing Surgery ማለት በኩላሊት ዉስጥ ያለዉን የካንሰር ዕጢ ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ ጤነኛዉ የኩላሊታችን ክፍል እንዲቀር የሚያደርግ ነዉ፡፡
ዕጢዉ ብቻ ሲወጣ ግን ምናልባት ሊቀሩ የሚችሉ የካንሰር ሴሎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ የሚቀሩትን ሴሎች የፓቶሎጂ ምርመራ በማድረግ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን መቀነስ ይቻላል፡፡

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ቅድመ ጥንቃቄስ ማድረግ ይቻል ይሆን?

ቀደም ብለን እንደ አጋላጭ ምክንያት ያነሳናቸዉን ጉዳዮች ለማስተካከል መሞከሩ እንደ ቅድመ ጥንቃቄ የሚነሳ ጉዳይ ነዉ፡፡
ስለዚህ ዉፍረት መቀነስ እንዲሁም ሲጋራ ማጬስ ማቆም ቅድመ ጥንቃቄ መሆኑን ዶክተር ማስረሻ ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም ግን ቀደም ብለን እንደገለጽነዉ የሚያጬስ እንዲሁም ከፍተኛ ዉፍረት ያለበት ሰዉ ሁሉ ደግሞ የኩላሊት ካንሰር ሊያጋጥመዉ ይችላል ማለት አይደለም፡፡

በእስከዳር ግርማ

ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *