በተለያዩ ከተሞች በኮንሶ፣ ጅማና አዲስ አበባ ከተማ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ የክልልና ፌዴራል ፖሊስ በጋራ በመሆን በተካሄደ ቁጥር የተለያዩ በርካታ ህገወጥ የወባ መድኃኒቶች መያዙን ባለስልጣን መስሪያቤቱ አስታውቋል፡፡
በደቡብ ክልል ኮንሶ ከተማ ላይ ብቻ ያልተመዘገቡ መድሀኒቶች እና በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምንም እውቅና የሌላቸው 29 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የወባ መድሀኒቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህገወጥ መከላከል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳምሶን አብርሀም ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
በጅማ ከተማ በተደረገ የቁጥጥር ሰራም 3 ሚሊዮን 1 መቶ 32 ሺህ የሚገመት የወባ እና ሌሎች ምድሀኒቶችን ጭምር በቁጥጥር ስር መዋሉን ነግረውናል፡፡
መድሀኒቶቹ በህገወጥ መልኩ በመኖሪያ ቤት ላይ ተከማችተው የተገኙ መሆናቸውን ያነሱት መሪ ስራ አስፈፃሚው ይህንን ድርጊት የፈፀሙ አካላት ላይ ቤቱ እንዲታሸግ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ህጋዊ ተቋም ሆነው መድሀኒት ቤት ያላቸው እና አከፋፋይ ድርጅቶች ህጋዊ ሽፋንን በመጠቀም ህገወጥ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም ቁጥጥር እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጲያ ምግብ እና መድሀኒት ባለስልጣን መስሪያቤትም ህገወጥ መድሀኒቶችን የመቆጣጠር እና የመከላከል ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም የትኛውንም ህገወጥ ተግባር ሲመለከት 8482 ነፃ የስልክ መስመር ላይ ጥቆማቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሐመረ ፍሬው
ሐምሌ12 ቀን 2016 ዓ.ም
