ሃምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረው የሃዋሳ ቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ክብረ በአል ያለምንም ጸጥታ ችግር እንዲከበር ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን ነው ከተማው ያስታወቀው፡፡
የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ከብሄራዊ ደህንነት ከፌደራል ፖሊስ እንደዚሁም ከሃዋሳ ከተማ ፖሊስ እንዲሁም ከከተማው ህዝብ የተውጣጣ ግብረ ሐይል ተቋቁሞ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
እንግዶች ወደ ሀዋሳ ሲመጡ እኛን ተማምነው በመሆኑ የሰላምና ፀጥታው ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥጠን እየሰራን ነው ለዚህም የፀጥታ ኃይሉ ሙሉ ዝግጅቱን አድርጓል ብለዋል።
ሀዋሳ የፍቅር የመቻቻልና የአንድነት ከተማ በመሆኗ ማንኛውም ሰው ወደ ከተማዋ ሲገባ እንደቤተሰብ ይታያል ያሉት ሃላፊው ከተማችንን የኢትዮጵያ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን የከተማ አስተዳደሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ይህ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረው የንግሥ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ነው አቶ አለማየሁ የተናገሩት፡፡
የበዓሉ ዕለት የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰትና የመንገድ መጨናነቅ እንዳይኖር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ያስታወቀው፡፡
ህብረተሰቡ የበዓሉን ሰላም የሚያውኩ አላስፈላጊ እንቅሰቃሴ የሚያደርጉ አካላትን ሲመለከት ለፖሊስና ለሌሎች በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ክልሉ መልዕክቱን አስተላልፏል።
በሄኖክ ወ/ገብርኤል
ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
