የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የዜጎች የኑሮ ሁኔታን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የሚያስችል ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በ2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገልጿል፡፡
የአገልግሎቱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሳፊ ገመዳ ለጣቢያችን እንደገለፁት ለዚህ ጥናት 600 ለሚጠጉ መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ሳፊ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት የሀገር ምጣኔ ሀብትና የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ያለበትን ደረጃ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
ይህ ጥናት የቤተሰብ ፍጆታ፣ የሰው ሃይል ስምሪት፣ የህዝብ ፍልሰትና የማህበራዊ ደህንነት አሰጣጥን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን የአንዳንድ ክልሎች የፀጥታ ሁኔታ ግን ለጥናቱ እንደስጋት የሚነሳ እንደሆነ አቶ ሳፊ ነግረውናል።
የጥናቱ ውጤት ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ውሳኔ ሰጪዎች እውቀትና መረጃን መሰረት አድርገው ውሳኔ እንዲያሳልፉ እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡
ለአለም አሰፋ
ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም
