ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እንዲመሰረት ዋናው መሰረት የነበረው ዋልያ ቁጥሩ እየቀነሰ መምጣቱን የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አስታውቋል፡፡
የፓርኩ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማሩ ቢያርግልኝ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በሰሜኑ የተከሰተው ጦርነት የቱሪስት ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር እና ለዋልያዎቹ መቀነስ ምክንያትም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዋልያዎችን ለመጠበቅ ሲባል እንደ ሳር ፣ደን እና ውሀ የመሳሰሉ ነገሮች ስለሚጠበቁ ዋልያዎች ከቀነሱ እና ከጠፉ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጎጂ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ዋልያ በአለም በኢትዮጰያ ሰሜን ተራሮች ብቻ የሚገኝ የዱር እንስሳ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የዋልያዎች ቁጥር እንዳይጠፋ እና ወደነበረበት ለመመለስ ፤ የሚገኙበት አካባቢ ላይ ከፍተኛ ክትትል የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ሀላፊው ቀደም ካሉት ግዜያት አሁን በፓርኩ የተሻለ የቱሪዝም ፍሰት መኖሩን አንስተዋል፡፡
ያለንበት ወቅት የፈረንጆች ዘመን መለወጫ ስለሆነ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት በርከት ያሉ ቱሪስቶች ፓርኩን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ከመስከረም 17 እስካሁን ባለው ግዜ ውስጥም ከ2500 በላይ ቱሪስቶች መቀበላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በአለም ቅርስነት የተመዘገበ ሀብታችን ስለሆነ ሁሉም ህብረተሰብ ትኩረት ሰጥቶ መንከባከብ አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሐመረ ፍሬው
ታኀሣሦ 23 ቀን 2017 ዓ.ም
