የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል፡፡
‘ከቃል እስከ ባህል’ በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ በርካታ ውሳኔዎች እና ወሳኝ አቅጣጫዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፤ ህወሓትን ጥሎ የተዋሐደው የብልጽግና ፓርቲ አባላት ቁጥር፤ ከ15 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲ የተመሰረተበት አምስተኛ ዓመት ሲያከብር ተናግረው ነበር፡፡
ኢትዮጵያን የሚመራዉ ብልጽግና ፓርቲ ፤ የፖለቲካ ምህዳርን ከማስፋት ፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ዲሞክራስያዊ እና ሰብዓዊ መብቶችን ከማስጠበቅ አንጻር ድጋፍም ተቃዉሞም እየተሰማበት ዛሬ ደርሷል።
ባለፉት ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ አሳካለሁ ብሎ ያላሳካዉ፤ ነገር አለመኖሩን ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የፓርቲዉ ባለስልጣናት እና አብዛኞች ደጋፊዎቹ ይናገራሉ።
ነቃፊዎቹ በበኩላቸው በፖርቲው የአመረር ዘመን የእርስ በእርስ ግጭቶች ተበራክተዋል፤ድህነት እና ጎስቁልና የነዋሪው ህዝብ ትከሻ አጎብጠዋል፡፡ከቦታ ቦታ መንቀሳስ ከባድ ሆኗል፡፡ ከተማ ስላማረ ሀገር አደገ ማለት አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ፓርቲው ጉባኤውን የሚያካሂደው ‘ከቃል እስከ ባህል’ በሚል መሪ ነው፡፡ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በርካታ ውሳኔዎች እና ሹም ሽሮች ይኖራሉ ተብሉ ይጠበቃል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በድምጽ ከሚሳተፉ 1,700 አባላት በተጨማሪ ከአገር ውስጥ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተወከሉ ግለሰቦች “በተጋባዥ እንግድነት” ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ የ15 የተለያዩ አገራት ፓርቲ ተወካዮችም ይሳተፉበታል ተብሏል።
የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ፤ የጠቅላላ ጉባኤ ማካሄጃ ጊዜ ከሶስት ዓመት መብለጥ እንደሌለበት ይደነግጋል። አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጋቢት 2014 ዓ.ም ያካሄደው ብልጽግና ፓርቲ፤ ሁለተኛው መደበኛ ስብሰባውን የሚያደርገው ከሁለት ዓመት ከ10 ወር በኋላ ነው።
ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም
