ከወለድ ነጻ ባንክ ወይም እስላማዊ ባንክ እንደመደበኛው የንግድ ባንክ አሰራር በርካታ አገልግሎት የሚሰጥ፣ ነገር ግን የሚሰራቸው ስራዎች ላይ ወለድ የማይሰጥና የማይቀበል መሆኑም ተነግሯል።
በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ በወለድ ባንክ ላይ መስራት ክልክል/ሃራም ነው የሚለው ቢታወቅም፣ አሰራሩን በተመለከተ እንዴትና ለማን የሚለው ላይ ግን የግንዛቤ እጥረት አለ ሲል ዘምዘም ባንክ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።
በዘምዘም ባንክ የስትራቴጂና ከስተመር ኤክስፔሪያንስ ማናጀርና ተወካይ የሆኑት አቶ በረከት አብደላ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከወለድ ነጻ ባንክ አገልግሎትን
ማንኛውም ሰው መርሁን ከተቀበለና ከተስማማ መጠቀም ይችላል ብለውናል። መርሁ ወለድን ጨምሮ በእስላማዊ ባንክ አሰራር ወንጀል ተብለው የተጠቀሱ ጉዳዮችን የሚከለክል ስለምሆኑም ነግረውናል።
ከእስልምና በተጨማሪ አብርሃማዊ ሃይማኖት የሚባሉት ክርስትና እና አይሁድ አራጣንና ወንጀልን የሚከለክሉ በመሆናቸው የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊጠቀምበት ይችላል ያሉት አቶ በረከት፣ ሆኖም ግን ሙስሊሞች ጭምር ስለ እስላማዊ ባንክ አሰራር በቂ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ለማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።
አሰራሩ ቀድሞ የገባቸው ሙስሊም ያልሆኑ የዘምዘም ባንክ ባለድርሻዎች ጭምር አሉ ሲሉም አክለዋል። ባንካቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራንም እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ በቂ ስላልሆነ ሌሎችም የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል።
ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ ከወለድ ነጻ ባንክ ወይም እስላማዊ ባንክ በሚገባው ልክ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሻራ እንዳያሳርፍ እንዳደረገው የተናገሩት አቶ በረከት አብደላ ማህበረሰቡ እንደ አማራጭ ባንክ ብቻ ሳይሆን እንደ ዋና አገልግሎት በመመልከት እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስአለም አበበ
ሚያዚያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም
