የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ከተወዳዳሪነት አንፃር ችግር ገጥሞታል ሲል የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ይህን በተመለከተ ሲናገሩ፣ የግብዐት ዋጋ ጭማሪ የኮንስትራክሽን ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ውስብስብ ችግር ውስጥ አስገብቶታል ብለዋል።
በተጨማሪም ከተቋማት አደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም፣ ከባለሙያ ብቃት ጋር የተያያዙና ሌሎችም ችግሮች በዘርፉ መስተዋላቸውን ተናግረዋል።
ለአጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት (GDP) ወደ 19 በመቶ የሚሆን አስተዋፅዖ የሚያበረክተውን የዚህን ዘርፍ ችግር ለመፍታት መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ነው ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የገለፁት።
ይህን የሚያግዝ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን የንግድ ትርዒት ከሰኔ 19፣ 2017 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስከ ሰኔ 21 ድረስ በሚከናወነው 3ተኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን የንግድ ትርዒት፣ የኢትዮጵያን ወደ 67 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የግንባታ ገበያን እና 395 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የመሠረተ ልማት ገበያን በመደገፍ ዘርፈ ብዙ ትብብር እና ጠንካራ ስትራቴጂካዊ የንግድ ትሥሥር እንደሚፈጥር ተገልጿል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትና ከግብርና ቀጥሎ ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ዘርፍ መሆኑንም ሚኒስትሯ አንስተዋል።
አዲስዓለም አበበ
ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም
