በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ቪዛ የቆይታ ጊዜ ወደ ሦስት ወር ማጠሩን አስታወቀ።
ኤምባሲው ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 3/2017 ዓ.ም. በኤክስ ገፁ ባሰፈረው መረጃ፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስደተኛ ባልሆኑ የቪዛ አመልካቾች ላይ ባደረገው የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ውሳኔው መተላለፉን ገልጿል።
በአዲሱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፖሊሲ መሠረት፤ “ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ለኢትዮጵውያን የሚሰጠው ቪዛ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል እና የሦስት ወር ቆይታ” እንደሚኖረው አስታውቋል።
ኤምባሲው በዚሁ የኤክስ ገጽ ልጥፉ ላይ ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. በፊት የተሰጡ ቪዛዎች ባሉበት እንደሚቀጥሉ ገልጿል።
ለንግድ እና ለጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የሚያገኙት ቪዛ “B1” እና “B2” በሚለው ምድብ ውድብ ውስጥ ይካተታል።
እስካሁን በነበረው አሰራር በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገቡ ተጓዦች የሚያገኙት ቪዛ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ነበር። በተጨማሪም የቪዛው የቆይታ ጊዜ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተደጋጋሚ ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ያስችል ነበር።
አሁን ይፋ የተደረገው ፖሊሲ የቪዛውን የቆይታ ጊዜ ወደ ሦስት ወር ከማሳጠር በተጨማሪ በአንድ ቪዛ ተደጋጋሚ ወደ አገሪቱ መግባትን ከልክሏል።
በአዲሱ ፖሊሲ ቪዛ የሚያገኙ ተጓዦች የቆይታ ጊዜ ባይጠናቀቅም እንኳ ከአሜሪካ ከወጡ በኋላ በዚያው ቪዛ ተመልሰው መግባት አይችሉም።
የአመልካቾችን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የማጣራት ሂደት ለማስፋት በዝግጅት ላይ እንዳለ ያስታወቀው አስተዳደሩ፤ ለተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጥ በጊዜያዊነት አግዶ ቆይቷል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ መልዕክት በሰፈረበት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በተላከ ማስታወሻ ላይ እገዳው “ተጨማሪ መመሪያ እስኪወጣ ድረስ” ይቆያል ተብሏል።
አስተዳደሩ የተማሪዎች አመልካቾች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን የማጣራት ስራ አጠናክሮ የሚሠራ ሲሆን ይህም በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ጽ/ቤቶች ላይ ትልቅ አንድምታ እንደሚኖረው ተገልጿል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
