በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ በተለያዩ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት የገንዘቦችን የመግዛት አቅም እየተፈታተነና አንዳንዶቹንም የመገበያያ ገንዘቦች ከጥቅም ውጭ እያደረጋቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፋይናስና የኢንቨስትመንት ባለሙያው አቶ ይርጋ ተስፋዬ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ ፤አሁንላይ በሳንቲሞች የሚሸመቱ ቁሶች ከጠፉ ሰነባብተዋል ብለዋል፡፡
ከአምስ እስከ ሃምሳ ሳንቲም ያሉ የመገበያያ ገንዘቦችም ከገበያ ወጥተዋል ማለት ይቻላልም ነው ያሉት፡፡
አቶ ይርጋ ገንዘቦቹ እየጠፉ ለመምጣታቸው ምክንያቱ የምርቶች ዋጋ መናር ነው ያሉ ሲሆን፤ ፍላጎትና አቅርቦትን ማቀራረብ አንዱ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘዴ ነው ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
ሌላኛው ጣቢያችን ያነጋገራቸው የፋይናስ ባለሙያው አቶ ጋማቹ ብረሃኑ፤የኢትዮጵያን የገንዘብ የመግዛት አቅም ማሳደግ እስካልተቻለ ድረስ ገንዘቦቻችን ላይ ቁጥር እየጨመርን ነው የምኔደው ብለዋል።
ይህ እንዳይሆን ከወዲሁ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ምርት መቀነስና የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።
የመሰረታዊ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ ንረት በዚህ የሚቀጥል ከሆነ አሁን ባሉት ገንዘቦቻችን ብዙ ጊዜ መቆት እንደ ማይቻልም አንስተዋል።
ይሄ ደግሞ እንደሌሎች ሃገራት የራስን ገንዘብ ከአገልግሎት አውጥቶ ዶላርን ወደ ማስገባት ያመራል ይህ ሁኔታ ደግሞ በመጨረሻ ሉአላዊነትን እስከመፈታተን ያደርሳል ሲሉ ጣቢያችን ያነጋገራቸው የፋይናስ ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
ልኡል ወልዴ
ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
