በሀገር ውስጥ ያሉ ተቋማት የሚያመርቱትን ምርትም ሆነ የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት በማስፈተሽ የተዓማኒነት ደረጃቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት የዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አክሊሉ ጌታቸው ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ ምርትን ወይም አገልግሎትን የጥራት ደረጃን ማስፈተሽና ማረጋገጫ መውሰድ እምብዛም የተለመደ አይደለም ብለዋል፡፡
አክሬዲቴሽን ግዴታ እንዳልሆነ የገለፁት አቶ አክሊሉ፣ ነገር ግን ለዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚዎች ላይ መተማመመንን ለማሳደር አገልግሎቱን ማግኘት ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተቋማቸው የሚሰጠው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት በዋናነት የሚሰራው አይሶ በሚያወጣቸው የጥራት ደረጃዎች ላይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አክሬዲቴት መሆን (የጥራት ማረጋገጫ ማግኘት) ከተወዳዳሪነት ባሻገር አትራፊነትን ያሳድጋል ያሉት የፅ/ቤት ሃላፊው፣ አገልግሎቱ የሚጠቀመው ዓለማቀፍ የጥራት ደረጃን (ስታንዳርድን) በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት የዓለማቀፎቹ የአይሶ እና የአይ ላይክ፣ እንዲሁም የቀጠናዊው አፍራክ አባል መሆኑን ጠቅሰው ተቋማቱም የአገልግሎቱን እንቀስቃሴ በየጊዜው እንደሚፈትሹ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት የዋና ዳይሬክተር ፅ/ቤት ሃላፊው አቶ አክሊሉ ጌታቸው፣ ዓለማቀፍ እውቅናው ለሀገራችን ተቋማት ምርትና አገልግሎት እንደፓስፖርት የሚያገለግል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተቋማት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን እንቅሰቃሴ እንዲጀምሩ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል፡፡
አዲስአለም አበበ
ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም
