የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ሊቀመንበር ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች አመቻቺነት የውክልና ሰነድ ተፈራርመዋል።
ባንኩ ለግንባታው የሚውል እስከ 8 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ የማሰባሰብ ሂደቱን ይመራል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፤ አየር ማረፊያዉ ከትራንስፖርት ማዕከልነት ባለፈ ኢትዮጵያን በ2035 በዓለም ከሚገኙ 20 ከፍተኛ የአቪዬሽን ማዕከላት መካከል እንድትሰለፍ የሚያደርግ ለውጥ ፈጣሪ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 20 በመቶ የሚሆነውን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህም 10 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል።
ማዕከሉ ከመዲናዋ በግምት 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በሁለት ዙር ይገነባል።
አዲስ የሚገነባዉ ይህ አየር ማረፊያ በመጀመሪያ በዓመት 60 ሚሊየን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ ወደ ሙሉ አቅሙ ከፍ ሲል 1መቶ10 ሚሊየን መንገደኞች ማስተናገድ ይችላል፡፡
አሁን በስራ ላይ የሚገኘዉ የቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ እስከ 25 ሚሊየን ተጓዦችን ማስተናገድ የሚችል ነዉ፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በ2029 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው።
ሀኒፍ ሀምዛ
ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም
