የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ከሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መሪዎች ጋር በጥምረት በአሜሪካ ላይ እያሴሩ ነው ሲሉ ወቀሱ።
ትራምፕ ይህንን ያሉት ቻይና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን ድል የተቀዳጀችበትን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ ታላቅ ወታደራዊ ትዕይንት ረቡዕ፣ ነሐሴ 28/ 2017 ዓ.ም ማካሄዷን ተከትሎ ነው።
በዚህ ታላቅ የወታደራዊ በዓል የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ 26 መሪዎች ተገኝተዋል።
ትራምፕ ለፕሬዚዳንት ሺ “በአሜሪካ ላይ በጋራ እያሴራችሁ ላላችሁት ለቭላድሚር ፑቲን እና ለኪም ጆንግ ኡን ሞቅ ያለ ሰላምታ አቅርብልኝ” ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም በቻይና፣ ሩሲያ እና ሌሎች አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአሜሪካ ተግዳሮት ጋርጧል መባሉን አጣጥለው ነበር።
ቻይና እና አጋሮቿ አሜሪካን ለመገዳደር አለም አቀፍ ጥምረት ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ ከቢቢሲ በቅርቡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ትራምፕ ሲመልሱ “አይሆንም፤ ቻይና ትፈልጋነለች” ብለዋል።
አክለውም “እንደምታውቁት እኔ ከፕሬዚዳንት ሺ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ቻይና ከኛ በላይ ትፈልገናለች። ይህ በፍጹም አይታየኝም” ብለው ነበር።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከአንድ የአሜሪካ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሩሲያ እና በቻይና መካከል የሚፈጠረው ጥምረት እንደማያሳስባቸው ተናግረው ነበር።
ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም
