የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ የክልሉ የትምህርት ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን እና ሰባት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች “እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት” እየተሰጡ እንዲቀጥሉ ወሰነ።
“ጊዜያዊ ነው” የተባለው ይህ አሠራር በዚህ ዓመት በቅድመ መደበኛ (ኬጂ) እና በአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የሚተገበር ሲሆን በየዓመቱ ወደ ሌሎች የክፍል ደረጃዎች እያደገ እንደሚሄድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ በክልሉ በሚነገሩ አፍ መፍቻ ቋንቋዎች ትምህርት መስጠት የጀመረው በ2001 ዓ. ም. ነበር።
የመማር ማስተማሪያ ቋንቋ ሆነው ከሚያገለግሉት አፍ መፍቻዎች መካከል ቤኒሻንጉልኛ፣ ጉምዝኛ፣ ሽናሽኛ እና ማኦኛ ይገኙበታል። ኮሞኛ፣ ጓምኛ፣ ኦሮምኛ እና አማርኛም ትምህርት ይሰጥባቸው ከነበሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መካከል ናቸው።
በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ሒሳብ እና የሳይንስ ትምህርት አይነቶችን በእነዚህ ቋንቋዎች የሚማሩ ሲሆን ሰባተኛ ክፍል ላይ የመማር ማስተማሪያ ቋንቋው እንግሊዘኛ ይሆናል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ ላሉ የወረዳ፣ ልዩ ወረዳ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በጻፈው ደብዳቤ ከዘንድሮ የ2018 ትምህርት ዘመን አንስቶ ይህ አሠራር መቀየሩን አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ ውሳኔው መተላለፉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በቢሮ ኃላፊው የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ላለፉት 17 ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን የቆየው አሠራር የተቀየረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ካቢኔ ባለፈው ወር መስከረም 10/2018 ዓ. ም. ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም
