የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በሀገሪቱ ላይ የጣሉትን ታሪፍ የሚተቹ ማስታወቂያዎች ከአየር ላይ ከዋሉ በኋላ ከካናዳ ጋር የሚያደርጉትን የንግድ ድርድር በአስቸኳይ ማቆማቸውን አስታውቀዋል።
በካናዳ መንግስት ድጋፍ የተደረገለት ይህ ማስታወቂያ፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገንን የአሜሪካ የወግ አጥባቂነት ተምሳሌት አድርጎ በመጥቀስ ታሪፍ እያንዳንዱን አሜሪካዊ ይጎዳል ሲል ዘግቧል።
ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያቸዉ ላይ ባጋሩት ጽሁፍ የተሰራው ማስታወቂያ ‹‹የሀሰት›› እና ‹‹አሳሳች›› ነው ብለዉ፤ የንግድ ንግግሮቹ “በዚሁ ተቋርጠዋል” ብለዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ባደረጉት ድርድር ከሜክሲኮ እና ከካናዳ ጋር በተደረገው የነፃ ንግድ ስምምነት መሰረት፤ በነፃ ንግድ ስምምነት ውስጥ የተካተቱ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ ፈቅደዋል፡፡
ነገር ግን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ከተመረጡ በኋላ፤ የአሜሪካን ታሪፍ የሚያቃልል ስምምነት ለመፈፀም ሞክረዉ ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት የታተመዉ ማስታወቂያዉ፤ የሬገን ድምጽ የኒውዮርክ ስቶክ ገበያን ባካተቱ ምስሎች እና በአሜሪካ እና በካናዳ ባንዲራ አጊጦ የተለቀቀ ነዉ፡፡
ሁኔታዉ በህግ አግባብ ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝም ተዘግቧል፡፡
በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ የጣሉትን አለም አቀፍ ታሪፍ ተከትሎ በኤክስ ገጹ ላይ ተመሳሳይ የሬጋንን ክሊፕ ተጠቅሞ ማስታወቂያ ለጥፏል ሲል የዘገበዉ ቢቢሲ ነዉ፡፡
ሀና ሰይፉ
ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም
