ኢትዮጵያ በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው እ.ኤ.አ በ2002 በናይጄሪያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነበር።
በወቅቱ በምድብ 1 ከአስተናጋጇ ናይጄሪያ፣ ጋና እና ማሊ ጋር ነበር የተደለደለችው።
የመጀመሪያ ጨዋታዋን በናይጄሪያ 3-0 ተሸንፋ ጀመረች።
በሁለተኛው ጨዋታ ከማሊ ጋር 2-2 ተለያይታ ለማንሰራራት ብትሞክርም በመጨረሻው ጨዋታ በጋና የደረሰባት የ3-0 ሽንፈት በ1 ነጥብና በ6 የጎል ዕዳ ከምድቧ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛ እንድትሰናበት አስገደዳት።
ሉሲዎቹ ከሁለት ዓመት በኋላ (2004) በደ/አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው 6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ የመሳተፍ ዕድል አገኙ።
የተደለደሉትም በምድብ 1 ከጋና፣ ዚምባቡዌ እና ደ/አፍሪካ ጋር ነበር።
የምድባቸውን የመጀመሪያ ጨዋታ ያደረጉት ከዚምባቡዌ ጋር 1-1 በመለያየት ነበር። የጎሏ ባለቤት ደግሞ አዲስ ፈለቀ ነበረች። በሁለተኛው ጨዋታ በጋና 2-1 ተረታን። ከሽንፈት ያልተረፍንባትን ጎል ያስቆጠረችው ቱቱ በላይ ነበረች።
በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በቱቱ በላይ እና ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ጎሎች አስተናጋጇን ደ/አፍሪካን 2-1 ረታን።
እናም በ4 ነጥብና ያለምንም የጎል ክፍያ ሙሉ 9 ነጥብ ይዛ ያጠናቀቀችውን ጋናን ተከትለን በሁለተኛነት ወደ ግማሽ ፍፃሜው ገባን።
(የተሳታፊ ሀገራት ብዛት ስምንት ብቻ መሆናቸውን ልብ ይሏል)
በግማሽ ፍፃሜው በናይጄሪያ 4-0 ተሸነፍን። በሌላኛው ጨዋታ ካሜሩን በጭማሪ ሰዓት ባስቆጠረችው ጎል ጋናን 1-0 ረትታ ከናይጄሪያ ጋር ለፍፃሜ አለፉ።
ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ እና ጋና በመደበኛውና በጭማሪው ሰዓት 0-0 ተለያየን። አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት 6-5 ተሸንፈን በአራተኛነት አጠናቀቅን።
በዛ ወሳኝ ጨዋታ ላይ ከጋና በኩል ሁለት ተጨዋቾች የፍፁም ቅጣት ምቱን ስተዋል።
በእኛ ቡድን በኩል ደግሞ ረውዳ አሊ፣ ሄለን ሰይፉ እና ብዙሃን እንዳለ ነበሩ የሳቱት። በወቅቱ ከ1-3 የወጡት ሀገራት በቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫ ያልፉ ስለነበር ኢትዮጵያ ለጥቂት ዕድሉ አመለጣት። ቢሆንም ግን በሀገሪቱ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እስከዛሬም ያልተደፈረ ከፍተኛ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል።
ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሱት በ2012 በኢኳቶሪያል ጊኒ በተካሄደው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።
ለዚህ ውድድር የደረስነው ከታንዛኒያ ጋር ባደረግነው የመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ አ/አ ላይ በሄለን ሰይፉ እና ቱቱ በላይ 2-1 ረትተን፤ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ ዳሬሰላም ላይ በብሩክታይት ግርማ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፈን (በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 3-1) እንደነበር አይዘነጋም።
በውድድሩ ላይ የተደለደልነው ከናይጄሪያ፣ አይቮሪኮስት እና ካሜሩን ጋር ነበር። በአይቮሪኮስት 5-0 ተሸንፈን ስንጀምር በናይጄሪያ 3-0 ተደገምን።
በመጨረሻው ጨዋታ ከካሜሩን 0-0 ተለያይተን በ1 ነጥብና በ8 የጎል ዕዳ የምድቡ መጨረሻ ሆነን ተሰናብተናል።
ዛሬስ ታንዛኒያን ረትተን ለአራተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እናልፍ ይሆን?
መልካም ዕድል!!
ምስጋናው ታደሰ
ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም
