ዘገባዎች እንደሚያሳዩት አሜሪካ ያረቀቀችው የሃያ ስምንት (28) ነጥብ የሰላም ማዕቀፍ በዋናነት የጦርነቱን መቋጫ ለማምጣት ሲባል ዩክሬን የተወሰነ መሬቷን እንድትተው እና በምትጠቀምባቸው የጦር መሳሪያዎች ላይ የሚጣለዉን ገደብ እንድትቀበል የሚያስገድዱ ሃሳቦችን ያካትታል።
በተለይም ዩክሬን መሬት እንድትሰጥ እና የጦር መሣሪያ ገደቦችን እንድትቀበል የሚያመለክተው ይህ የአሜሪካ ረቂቅ ከሩሲያ የቀረቡ የቀድሞ ጥያቄዎች ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ዘገባዎቹ ጠቁመዋል።
ይህ ዕቅድ በዋሽንግተን በኩል የቀረበ ቢሆንም በውስጡ የተካተቱት ቁልፍ ነጥቦች የሩሲያን ፍላጎት ያማከሉ ሊሆኑ እንደሚችል ይጠበቃል።
የዜና አውታሮች እንደዘገቡት ከሆነ ስምምነቱ ኪቭ አሁን በሩሲያ ቁጥጥር ስር ያሉ አንዳንድ መሬቶችን በቋሚነት እንድትተው የሚያስችል ስምምነት እንድትቀበል ሊጠይቅ ይችላል።
ወደፊት ዩክሬን የምታገኛቸው የጦር መሳሪያዎች አይነትና ብዛት እንዲሁም የጥቃት ርቀት ላይ ገደቦች እንዲቀመጡ የታሰበ ሲሆን፤ ይህም ሩሲያ የደህንነት ስጋት እንዳይሰማት ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ሩሲያም ሆኑ ዋሽንግተን የመረጃውን ትክክለኛነት አላረጋገጡም።
ከፍተኛ የፔንታጎን ባለሥልጣን “ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረግ ጥረት ላይ ለመነጋገር” ዩክሬን መግባታቸውን የአሜሪካ ጦር አስታዉቋል፡፡
በአሜሪካ ጦር ዋና ጸሀፊ ዳን ድሪስኮል የተመራው የልዑካን ቡድን ሐሙስ ዕለት በኪቭ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ያገኛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል እንደ ቢቢሲ ዘገባ።
ሱፊያን አህመድ
ህዳር 11/2018 ዓ.ም
