በካፒታል ገበያው እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያለመው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ፓሊሲ አውጭዎች፣ የታወቁ የፋይናንስ ዘርፍ ምሁራንና ባለሙያዎችን ያሰባሰበ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት የካፒታል ገበያውን የተመለከቱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ለውይይት ይቀርቡበታል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኽልቁን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
በተመሳሳይም ከአለም አቀፍ ተቋማት መካከል የአለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና ዩኤንዲፒ (UNDP) ተወካዮች በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ ተሳትፈዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ጉባኤው የካፒታል ገበያው ቁጥጥር እንዲጠነክርና የኢንቨስትመንት አቅሙ እንዲጎለብት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በተጨማሪም ጉባኤው ጤናማ የፋይናንስ ስርአት እንዲኖር ከማስቻሉም ባሻገር፣ አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያለውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በጉባኤው የሚነሱት ሀሳቦችና ልምዶች ለገበያው ጥንካሬና ቁጥጥር ሁነኛ ግብአት ሆነው እንደሚያገለግሉም ተመልክቷል።
ለዓለም አሰፋ
ህዳር 23/2018 ዓ.ም
