የኢትዮጵያ መንግስት በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ከፍ ለማድረግና የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።
በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ተወካይ ኢንጂነር ባህሩ አሰፋ፤ ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) ወደ ብሔራዊ ግሪድ በመግባቱ እና ከውሃ ኃይል በተጨማሪ ከነፋስ፣ ከፀሐይ እና ከጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት ፕሮጀክቶች በመገንባት ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል አቅሟን ለመጠቀም እየጣረች እንደሆነም አንስተዋል።
ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ከፍተኛ የፋይናንስና የግብዓት ችግሮች እንደሚገጥሙት ተገልጿል።
በተለይም የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከጠቅላላ ወጪያቸው ከ60% እስከ 70% የሚሆነው በውጭ ምንዛሪ የሚሸፈን በመሆኑ፣የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፕሮጀክቶችን በተፈለገው ፍጥነት ለማከናወን ዋና እንቅፋት ሆኗል።
የብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP) እስከ 2030 ድረስ 75% የሚሆነው ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት እንዲያገኝ ያለመ ሲሆን፣ ይህንን ግብ ለማሳካት ከብሔራዊ ግሪድ በተጨማሪ አነስተኛ ግሪዶችን፣ ገለልተኛ የኃይል ስርዓቶችን እና የሶላር የቤት ስርዓቶችን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮች እየተተገበሩ ናቸው ሲሉም ኢንጂነሩ ገልጸዋል።
በቅርቡ በተካሄደ የኢነርጂ ኮንፈረንስ ላይ የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባን የማሳደግ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ተሰጥቷል፤ ይህም የኃይል ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ይረዳልም ተብሏል።
ይህ ኮንፈረንስ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሰባሰብ የፖሊሲ ልምድ ልውውጥ ለማድረግና የፋይናንስ አማራጮችን ለመፍጠር ያለመ ነበር።
መንግስት የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማጎልበት እየሰራ ቢሆንም፣ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ብቃትን በበቂ ሁኔታ ያለመገንባት የግብዓት ችግሮችን እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።
ለአለም አሰፋ
ህዳር 25/2018 ዓ.ም
