የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ሁሉንም የስፖርት ውድድር ውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃዶች ከታህሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መሰረዙ ተሰምቷል፡፡
የፈቃድ ስረዛው በውርርድ እና በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በተካሄደ አገር አቀፍ ጥልቅ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ድርጅቱ አሳውቋል፡፡
ውሳኔው በስራ ላይ ባሉትና ቀደም ሲል በይፋ በታገዱት በሁሉም የውርርድ ድርጅቶች በእኩልነት ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሂደት ላይ ያለው ምርመራ በዘርፉ ውስጥ የተንሰራፋ ህገ-ወጥ አሰራር፣ የፈቃድ ውል ጥሰት እና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሚሆኑ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች እንዳሉ በግልጽ አመላክቷል።
ለስፖርት ውርርድ ድርጅቶች እና ሲስተም ኦፕሬተሮች/አቅራቢዎች ከታህሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአካል፣ በዲጂታል ወይም በሌላ መንገድ የሚካሄድ ማንኛውንም የውርርድ ሥራ እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ሁሉም የገንዘብ ማስገቢያ መንገዶች አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙም ታዟል።
አዲስ ውርርድ መቀበል ፈጽሞ አይቻልም ተብሏል።
ታህሳስ 06/2018 ዓ.ም
