ቻይና ታይዋንን ካጠቃች ሩሲያ አውሮፓን በሥራ ልትጠምድ ትችላለች ሲሉ ነዉ የኔቶ መሪ ማስጠንቀቂያ የሰጡት፡፡
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩቴ፤ ቻይና በታይዋን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ካደረሰች ሩሲያ የአውሮፓን ትኩረት ልትከፋፍል እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
ጸሐፊዉ ለጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ቤጂንግ እና ሞስኮ የጠበቀ ትስስር እንዳላቸውና በኢንዶ-ፓሲፊክ ቀጣና የሚፈጠር ማንኛውም ውጥረት ለአውሮፓ ደህንነት ቀጥተኛ መዘዝ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።
በቻይና እና በሩሲያ መካከል ያለውን ዓለም አቀፋዊ ትስስር እናዉቃለን፡፡ቻይና ታይዋን ላይ አይኗን ጥላለች ወታደራዊ እርምጃ ከወሰደች፤ ሩሲያን እዚህ አውሮፓ ውስጥ እኛን በሥራ እንድታጠምደን ጫና ታደርግባታለች ብዬ አምናለሁ ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ኔቶ የመከላከል አቅሙን በአስቸኳይ ማጠናከር እንዳለበት ገልጸው፤ ሞስኮ አሁንም ከፍተኛ ኪሳራዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን አንስተዋል፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ፑቲን ናቸው ያሉት ጸሀፊዉ፤እርሳቸው 1.1 ሚሊየን የሚሆነውን የገዛ ህዝባቸውን ለመሰዋት ዝግጁ ናቸው። በዚህ ዓመትም ያገኙት ውጤት በጣም አነስተኛ ነው፤ ከዓመቱ መጀመሪያ ጋር ሲነጻጸር የተቆጣጠሩት የዩክሬን ግዛት ከ1 በመቶ ያነሰ ነው ሲሉ አክለዋል።
ሊደረጉ ስለሚችሉ የወታደር መዋጮዎች ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንም አረጋግጠዉ፤ በርካታ የአውሮፓ አገራት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወታደሮችን ለማዋጣት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሩቴ ዋሽንግተን ከአውሮፓ ጋር ያላትን ግንኙነት ልታቋርጥ ትችላለች የሚለውን ግምት ውድቅ በማድረግ፤ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ሚና አወድሰዋል።
ትራምፕ ለዚህ ጉዳይ ፍጹም ቁርጠኛ መሆናቸውን መናገር አለብኝ። ትኩረታቸው ይህንን ጦርነት ማስቆም ላይ ነው።
ፑቲንን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት የቻሉት ብቸኛው ሰው እርሳቸው ናቸው፤ በመጨረሻም ሰላም እንዲያወርዱ ሊያስገድዷቸው የሚችሉት እርሳቸው ብቻ ናቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል እንደ አናዶሉ ዘገባ።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 13/2018 ዓ.ም
