ትራምፕ “ፑቲን ዩክሬን ስኬታማ እንድትሆን ይፈልጋሉ፤ በዝቅተኛ ዋጋ ነዳጅ ለማቅረብም ፈቃደኛ ናቸው”አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ ፑቲን ለዩክሬን “መልካም ምኞት” እንዳላቸውና አገሪቱ ከጦርነት በኋላ መልሳ እንድትገነባ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት በፍሎሪዳው ማር-አ-ላጎ ከመኖሪያ ቤታቸው የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪን ባገኙበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ሩሲያ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ ይጠበቃል ብለዋል።

“ፑቲን ዩክሬን ስኬታማ እንድትሆን ይፈልጋሉ። ይህ ምናልባት እንግዳ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ፑቲን ዩክሬን እንድትበለጽግ ያላቸው ስሜት በጣም ለጋስ ነው” ብለዋል ትራምፕ።

ሩሲያ ለዩክሬን የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና ሌሎች የኃይል አቅርቦቶችን “በጣም በተመጣጣኝ ዋጋ” ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ከፑቲን ጋር ከአንድ ሰዓት በላይ የቆየ “ውጤታማ” ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ረዳት የሆኑት ዩሪ ኡሻኮቭ እንደገለጹት፣ ሁለቱ መሪዎች የሰላም ሂደቱን ለማገዝ በጸጥታ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሁለት የሥራ ቡድኖች እንዲቋቋሙ ተስማምተዋል።

ሆኖም ሩሲያ በዩክሬን እና በአውሮፓውያን የቀረበውን የጊዜያዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ውድቅ አድርጋለች። ፑቲን እንዲህ ዓይነቱ ስምምነት “ለዩክሬን ጦር ዳግም መደራጃ ጊዜ ይሰጣል” በሚል ስጋት፣ ዘላቂ መፍትሔ ላይ ያተኮረ ስምምነት እንደሚመርጡ ተገልጿል።

ይህ በትራምፕ እና በፑቲን መካከል የተደረገው ግንኙነት፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት አዲስ የዲፕሎማሲ መንገድ ሊከፍት እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።

ልዑል ወልዴ

ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *