ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በኪጋሊ መንግስት የሚደገፈው የኤም23 ታጣቂ ቡድን አዲስ ጥቃት ከሰነዘረበት ከታህሳስ ወር መጀመሪያ ጀምሮ፤ ሩዋንዳ በምስራቃዊ ኮንጎ ከ1 ሺህ 5መቶ በላይ ሲቪሎችን ገድላለች ስትል ከሳለች፡፡
የኮንጎ መንግስት ባወጣው መግለጫ፤ ይህ የሟቾች ቁጥር ከሲቪል ማህበረሰቡ የተገኘ መሆኑንና በሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም በመንግስት መስሪያ ቤቶች መረጋገጡን ገልጿል።
የኮንጎ ባለስልጣናት አዲሱን የጥቃት ማዕበል በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ግልጽ የጥቃት ተግባር እንዲሁም ከባድና ተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት ነዉ ሲሉ ገልጸውታል።
የኤም23 አማፂያን ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በደቡብ ኪቩ የምትገኘውን ቁልፍ ከተማ ኡቪራን የተቆጣጠሩ ሲሆን፤ይህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ቡሩንዲ እንዲሰደዱ አድርጓል።
ኤም23 ይህን አዲስ ጥቃት የጀመረው የኮንጎ እና የሩዋንዳ መንግስታት በአሜሪካ አጋዥነት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በፈረንጆቹ ታህሳስ 4 በፈረሙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ከሆነ በደቡብ ኪቩ በቅርቡ በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት ወደ 5መቶ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 24/2018 ዓ.ም
