በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ በተደጋጋሚ ይስተዋል የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ 600 ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በአቢጃታ ሐይቅ ላይ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በአቢጃታ ሐይቅ ከመጠን ያለፈ የውሀ ሙሌት ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ወድቀው፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያውም በውሃ ተጥለቅልቆ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ነበር፡፡
ይህ ክስተት ከአካባቢው ከባድ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምሰሶ ሲቆም በንፋስ ሲወድቅና በመሬቱ ጨዋማነት ወዲያው ሲበላ፣ ተቋማችንም ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ ጥገና ሲያከናውን በርካታ ጊዜያት ማለፉ ተገልጿል፡፡
በዚህም 7 ከብረት የተሰሩ ምሰሶዎች በውሃ ውስጥ፣8 ተጨማሪ የእንጨት ምሰሶዎችን በመሬት ውስጥ በድምሩ የ15 ምሰሶዎች ተከላ በማከናወን 600 ሜትር ርዝመት ያለው መስመር በአቢጃታ ሻላ ሀይቅ ላይ መዘርጋት መቻሉን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
በዚህም የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ ተደርጎ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከማድረግ ባሻገር በአካባቢው ለሚገኙ 1መቶ50 አባወራዎች ብርሀን እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ብላል፡፡
ይህ የኃይል መስመር ዝርጋታ ቢያንስ ለ15 ዓመት የሚያገለግል የብረት ምሰሶ ተከላ የተከናወነበት በመሆኑ ኢንዱስትሪውን ቀጣይነት ያለው የኃይል አቅርቦት ያረጋግጣል፤ አገልግሎቱንም ተደጋጋሚ ከሆነ የጥገና ስራ ያሳርፋል ተብሎ እንደሚታመን ተገልጿል፡፡
ጥር 04/2018 ዓ.ም
