በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ ዋንጫ ቅዳሜና እሁድ ከሚደረጉት የደረጃና የፍፃሜ ጨዋታዎች በፊት 120 ጎሎች በመቆጠራቸው በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው የጎል ብዛት የተመዘገበበት አዲስ ሆኗል።
ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2019 በግብፅ ተካሂዶ በነበረው ውድድር ተመዝግቦ የነበረውን የ102 ጎሎች ክብረ ወሰን የሰበረ ሆኗል።
ለዚህ የጎል ብዛት መጨመር የአህጉሪቱ ታላላቅ ሀገራት ቀዳሚውን ሚና ተጫውተዋል። ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮ እና ኮትዲቩዋር ጠንካራ የማጥቃት ብቃታቸውን ሲያሳዩ አዳዲስ ተተኪ ተሰጥኦዎችም ከቀድሞ ኮከቦች እኩል ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል።
ለዚህ አስደናቂ ክብረ ወሰን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ፣ የግብፁ መሐመድ ሳላህ እና የናይጄሪያውን ቪክቶር ኦሲሜን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ተጠቃሾች ናቸው።
ዲያዝ በ5 ጎሎች የከፍተኛ ጎል አግቢነቱን እየመራ ይገኛል። ሳላህ እና ኦሲሜን ደግሞ እያንዳንዳቸው 4 ጎሎችን አስቆጥረዋል። ሁለቱም ነገ (ቅዳሜ) ለ3ኛ ደረጃ በሚደረገው ጨዋታ ላይ ስለሚሳተፉ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ሽልማቱን ለማሸነፍ ወይም ለመጋራት አሁንም ዕድሉ አላቸው።
የአፍሪካ ዋንጫው ሊጠናቀቅ የሚቀሩ ሁለት ጨዋታዎች በመኖራቸው ይህ የጎል ብዛት ክብረ ወሰን ሊጨምር ይችላል።
ምስጋናው ታደሰ
ጥር 8/2018 ዓ.ም
