ኢትዮ ቴሌኮም 85 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘሁ አለ

ኩባንያው የዕቅዴን 81 በመቶ ነው ያሳካሁት ያለ ሲሆን፥ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ግን የ37 በመቶ ዕድገት አስመዝግቤያለሁ ብሏል።

የደንበኞቹን ቁጥርም 87.1 ሚሊየን ማድረሱን አስታውቋል።

ተቋሙ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ የ8.2 በመቶ ዕድገት በማሳየት የደንበኞቹን ቁጥር 87.1 ሚሊየን ማድረሱን የገለፁት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው።

የተቋማቸውን የ6 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፥በነሐሴ ወር 2017 ይፋ በተደረገው አዲስ የሶስት ዓመት “ቀጣዩ አድማስ” በተሰኘው ስትራቴጂ፤ የደንበኞቹን ቁጥር ለመጨመር ዕቅድ ይዞ እንደነበር አስታውሰዋል።

ኩባንያው የቴሌብር ደንበኞቹንም ቁጥር 58.61 ሚሊየን ማድረሱን ገልፀዋል።

በ6 ወራት ውስጥ በቴሌብር የተደረገ የኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ዝውውርም 1.94 ትሪሊየን ብር ደርሷል ነው ያሉት።

ኩባንያው በነሐሴ ወር 2017 አዲስ የሶስት ዓመት “ቀጣዩ አድማስ” ሲል የሰየመውን ስትራቴጂ ይፋ ባደረገበት ወቅት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፥ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ብናውቅም መፍትሄዎችም አዘጋጅተናል ብለው ነበር።

በዚህ ሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥም የቴሌብር ደንበኞቹን ቁጥር 75 ሚሊየን ለማድረስ ማሰቡን ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።

በአገራችን አጠቃላይ ለፋይዳ መታወቂያ ከተመዘገቡ ወደ 32 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች፥ በ1 ዓመት ከ8 ወር ጊዜ ውስጥ 21.5 ሚሊየኑ በኢትዮ ቴሌኮም ምዝገባ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።

በዚህ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ደግሞ 10.11 ሚሊየን ሰዎች ለፋይዳ መመዝገባቸውን ገልፀዋል።

እስከዳር ግርማ

ጥር 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *