የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ሁኔታው ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት አስጊ ወቅት መሆኑን በመግለጽ ስጋቱን አሳውቋል፡፡
ሩሲያ እና አሜሪካም ወደ ውይይት እንዲመለሱ አሳስቧል።
ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የነበራት የመጨረሻው የአቶሚክ ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ስምምነት ሊያበቃ በመሆኑ ማሰማራት የምትችለውን የኒውክሌር መሳሪያዎች ቁጥር በሚመለከት ‹‹ከእንግዲህ በገደቦች አልገደድም››ብላለች።
እንደ አዉሮፕያዊያኑ በ2010 የተፈረመው ይህ ስምምነት በዛሬዉ ዕለት ያበቃል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ አሜሪካ በስምምነቱ ውስጥ ያሉትን የሚሳኤል እና የኒውክሌር መሳሪያ ገደቦች ለተጨማሪ 12 ወራት ለማክበር ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ ምላሽ አልሰጠችም።
ስምምነቱ ለ10 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፤ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩት ባራክ ኦባማ እና ከ2008 እስከ 2012 የሩሲያ ፕሬዝዳንት ሆነው ባገለገሉት የፑቲን የቅርብ አጋር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የተፈረመ ነበር።
ስምምነቱ በ2011 በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሥልጣን ከያዙ በኋላ በ2021 ለተጨማሪ አምስት ዓመታት ተራዝሞ ነበር።
የስምምነቱ ማብቃት ሞስኮም ሆነች ዋሽንግተን የሚሳኤል ቁጥራቸውን እንዲጨምሩ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር መሳሪያዎችን እንዲያሰማሩ ነፃ ያደርጋቸዋል ያለዉ አልጀዚራ ነዉ፡፡
እስከዳር ግርማ
ጥር 28/2018 ዓ.ም
