የቀድሞው ልዑል አንድሪው በኤፕስታይን ፋይሎች ውስጥ በተገለጹ መረጃዎች ምክንያት በእንግሊዝ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ወይም ልዑል አንድሪው በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ እያሉ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ጥርጣሬ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህም በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ አንድ የእንግሊዝ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል በፖሊስ ሲያዝ የመጀመሪያው ነው።

የንጉሡ ወንድም በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ከሟቹ የሕፃናት ጾታዊ ጥቃት ፈጻሚ ጄፍሪ ኤፕስታይን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በሚመረምረው የፖሊስ አካል ነው።

ይህ የሆነው ልዑል አንድሪዉ በ2010 የብሪታንያ ልዩ የዓለም አቀፍ ንግድ መልዕክተኛ በነበሩበት ወቅት፤ ሚስጥራዊ የንግድ መረጃዎችን ለሟቹ ባለሀብት ኤፕስታይን ልከዋል የሚሉ ዘገባዎችን ተከትሎ ነው።

መረጃው ይፋ የሆነው ባለፈው ወር በአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት ከወጡት በሚሊየን የሚቆጠሩ የ‹‹ኤፕስታይን ፋይሎች››መካከል በሁለቱ ሰዎች መካከል በተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች መሆኑ ተገልጿል፡፡

የእንግሊዝ ፖሊስ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ከፍተኛ የሕዝብ ፍላጎት እንረዳለን፣ እናም በተገቢው ጊዜ ተጨማሪ መረጃዎችን እንሰጣለን ብሏል።

ፖሊስ በተጨማሪም ቀድሞ ልዑሉ ይኖርባቸው የነበሩ ሁለት ቤቶችን እየፈተሸ መሆኑን ገልጿል።

ንጉሥ ቻርልስ በወንድማቸው መታሰር የተሰማቸውን ስጋት ቢገልጹም፤ለምርመራው ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሰጡ ገልጸዉ ‹‹ሕጉ የራሱን መንገድ መከተል አለበት›› ብለዋል።

የቀድሞው ልዑል ሊታሰሩ የሚችሉት ከፍተኛው ጊዜ 96 ሰዓታት ሲሆን፤ ይህም ከከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች እና ከፍርድ ቤት የሚሰጥ ተጨማሪ ፈቃድ ይጠይቃል።

ኤፕስታይን በ2019 በኒውዮርክ አቃቤ ሕግ በወሲብ ንግድ ዝውውር ክስ ተመስርቶበት በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረ ሲሆን፤በፍርድ ቤት ክርክሩን እየተጠባበቀ ሳለ በእስር ቤት ውስጥ የራሱን ሕይወት አጥፍቷል።

ሀና ሰይፉ

የካቲት 13/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *