ቻድ የአምስት ወታደሮቿን ሕይወት ከቀጠፈው ግጭት ጋር በተያያዘ ከአጎራባች ሱዳን ጋር ያለውን ድንበር ዘግታለች።
የቻድ መንግሥት ድንበሩ መዘጋቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹በሱዳን ግጭት ውስጥ ባሉ ኃይሎች የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች እና ጥሰቶች››መሆናቸውን ገልጿል።
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ቻድ ግዛት ሲዛመትና ለሰው ሕይወት መጥፋት እንዲሁም ለንብረት ውድመት ምክንያት ሲሆን ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
አንድ የቻድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት፤ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ለመንግሥት ታማኝ በሆኑ ወታደሮች መካከል ያለው ውጊያ ቲኔ በተባለች የድንበር ከተማ ውስጥ ተከስቷል።
ከተገደሉት አምስት ወታደሮች በተጨማሪ ሦስት ንጹሐን ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ሌሎች አሥራ ሁለት ደግሞ ቆስለዋል።
ይህ የሆነው የሱዳን ጦርነት ወደ አራተኛ ዓመቱ ሊገባ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት ነው።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለጻ፤ የሱዳን ጦርነት በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ እና ትልቁን የረሃብ ቀውስ አስከትሏል።
ግጭቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችንም አፈናቅሏል።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 17/2018 ዓ.ም
