በኢራን የሚንቀሳቀሱ አምስት የኩርድ ቡድኖች ጥምረት በመፍጠር ጦርነት አወጁ

በኢራን የሚንቀሳቀሱ አምስት ታዋቂ የኩርድ የፖለቲካ እና የታጠቁ ቡድኖች፣ ለአሥርተ ዓመታት የነበራቸውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው ታሪካዊ የተባለለትን የአንድነት ስምምነት መፈረማቸውን አስታውቋል።

ቡድኖቹ “አንድነት ለድል” በሚል መሪ ቃል በፈጠሩት በዚህ አዲስ ጥምረት፣ የኢራኑን ‘የኢስላማዊቷን ሪፐብሊክ’ አገዛዝ በወታደራዊ ኃይል ለመጣል ይፋዊ ጦርነት አውጅዋል።

ይህ አዲስ ጥምረት የተመሰረተው ቡድኖቹ በትጥቅ ትግልና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻቸው የጋራ ግንባር ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ነው።

ጥምረቱ በጋራ በሚመሩት ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች ወደ ኢራን ምድር ዘልቀው ለመግባት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል።

እንደ CNN እና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ፣ የዚህ ጥምረት መፈጠር በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ላይ አዲስ ውጥረት አንግሷል።

የኢራን መንግስት ለዚህ እንቅስቃሴ ፈጣን ምላሽ መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ የኢራን አብዮታዊ ዘበኛ (IRGC) በኩርድ ይዞታዎች ላይ የድሮን ጥቃቶችን መጀመሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ይህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኢራን ውስጥ ለወራት የቀጠለውን የውስጥ ተቃውሞ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ሊቀይረው ይችላል የሚል ስጋት በዓለም አቀፍ ተመልካቾች ዘንድ አሳድሯል።

የኩርድ ቡድኖቹ በበኩላቸው፣ የኢራን አገዛዝ እንዲያበቃና የብሔረሰቦች መብት እንዲከበር በትጥቅ ትግሉ እንደሚገፉበት ገልጸዋል።

ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ወደሆነ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኢራን መንግስት ጥምረቱን ለመመከት ተጨማሪ ኃይሎችን ወደ ድንበር አካባቢዎች እያሰማራ መሆኑ ተነግሯል።

ልዑል ወልዴ

የካቲት 25/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *