የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኬር ኢትዮጵያ (CARE Ethiopia) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን አዲስ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ስትራቴጂ በአዲስ አበባ በይፋ አጽድቋል።
ይህ ስትራቴጂ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የሚታዩ የሥርዓተ ጾታ ክፍተቶችን ለመሙላትና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የታለመ መሆኑ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እንደተናገሩት፣ እናቶችና ሴቶች በዘርፉ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት በመሆናቸው ሚኒስቴሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በተለይም በገጠር አካባቢዎች ሴቶች ውሃ ለመቅዳትና ለማገዶ የሚሆን ኃይል ፍለጋ የሚጋለጡበትን ከፍተኛ ጫና ለመቀነስ ስትራቴጂው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
ስትራቴጂው እ.ኤ.አ በ2022 እና በ2024 በተካሄዱ ጥናቶች ላይ ተመስርቶ በባለሙያዎችና በቴክኒክ ኮሚቴዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኬር ኢትዮጵያ የፕሮግራም ማናጀር ወይዘሮ ፍትሕ ደምበላሽ አማካኝነት በዕለቱ ቀርቧል።
ስትራቴጂው በዋናነት በሦስት ምሰሶዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን ፤ እነሱም ሴቶች የውሃና ኢነርጂ አገልግሎቶችን በእኩልነት እንዲያገኙ ማድረግ፣ በውሳኔ ሰጪነትና በአመራር ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም በዘርፉ ከሚፈጠሩ የሥራና የሥልጠና ዕድሎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ናቸው።
ይህ አዲስ መመሪያ በሰነድ ደረጃ የተቀመጡ ዕቅዶች እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ በተግባር የሚተረጎሙበትን የአሰራር ሥርዓት የዘረጋ ሲሆን፣ ትክክለኛ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለሴቶች፣ ለሕፃናትና ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን የበጀት ድልድል ለማድረግ እንደሚያግዝም ተገልጿል። በመጨረሻም ስትራቴጂው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያለውን የሥርዓተ ጾታ መምሪያ አቅም በማጠናከር ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲኖር እንደሚያስችል ተጠቁሞ፣ ለስኬታማነቱም የባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
ለዓለም አሰፋ
መጋቢት 09/2018 ዓ.ም
