በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ ዘጠኝ አገራት ውስጥ ከ40 በላይ የኃይል ሀብቶች በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኤጀንሲ መግለጹን የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ፋቲህ ቢሮል እንደተናገሩት፤ የደረሰው ጉዳት ግጭቱ ካበቃ በኋላም እንኳ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚፈጠረውን መስተጓጎል ሊያራዝም ይችላል።
የነዳጅ ማጣሪያዎች እና የቧንቧ መስመሮች በድጋሚ ወደ ሥራ ለመመለስ የተወሰነ ጊዜ ይወስድባቸዋል ብለዋል።
ቢሮል እንደገለጹት፤ ከሦስት ሳምንታት በላይ የዘለቀው ውጊያ አጠቃላይ የኢነርጂ አቅርቦት ሰንሰለቱን ያደናቀፈ ሲሆን፤በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚደረገውን የጭነት መርከቦች ጉዞ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አስቁሟል።
ቢሮል እስያ በክልሉ የኃይል አቅርቦት ላይ ጥገኝነት ስላላት በተለየ ሁኔታ እንደምትጎዳ አስጠንቅቀዋል።
እያንዳንዱ አገር መጀመሪያ የራሱን የአገር ውስጥ ጥቅም ይመለከታል፤ ነገር ግን ያለ በቂ ምክንያት የሚደረጉ ከባድ የወጪ ንግድ ገደቦች አዎንታዊ ውጤት ላይኖራቸው ይችላል ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ የአቅርቦት እጥረቱን ለማቃለል 400 ሚሊየን በርሜል ድንገተኛ የነዳጅ ክምችት ለመልቀቅ ማቀዱን የገለጹት ቢሮል፤መስተጓጎሉ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ ክምችት ሊለቀቅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በቀን ወደ 20 ሚሊየን በርሜል ገደማ ነዳጅ የሚያልፍበት ይህ ወሽመጥ መዘጋቱ፤ የትራንስፖርት ወጪን የጨመረ ሲሆን የዓለም የነዳጅ ዋጋም እንዲንር አድርጓል።
በኢራን ላይ በተከፈቱት የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃቶች በወቅቱ የነበሩትን የበላይ መሪ አሊ ካሜኒን ጨምሮ ቢያንስ 1 ሺህ 3መቶ ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል።
ኢራንም እስራኤልን፣ ዮርዳኖስን፣ ኢራቅን እና የአሜሪካ የጦር ሰፈር የሚገኘባቸዉን የባሕረ ሰላጤዉን አገራት በድሮን እና በሚሳዔል ጥቃቶች በመምታት የአጸፋ ምላሽ ሰጥታለች።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
