ፍቅረኛውን ትምህርት ቤት ለማድረስ አውቶብስ የሰረቀው የ15 ዓመቱ ታዳጊ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

በጀርመን ቪዝባደን ከተማ የሚኖር አንድ የ15 ዓመት ታዳጊ፣ የ14 ዓመት ፍቅረኛውን ትምህርት ቤት ለማድረስ ሲል የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ሰርቆ 130 ኪሎ ሜትር ካሽከረከረ በኋላ በፖሊስ ሊያዝ ችሏል።

ታዳጊው ንጋት 12 ሰዓት ገደማ ወደ ግቢው ዘልቆ በመግባት የአውቶብሶችን መቆጣጠሪያ ዋና ቁልፍ ካገኘ በኋላ ተሽከርካሪውን ይዞ መውጣት የቻለ ሲሆን፣ በወቅቱ በስፍራው የነበሩ የጥበቃ ሰራተኞች ድርጊቱን በካሜራ ቢመለከቱም አሽከርካሪው የድርጅቱ ሰራተኛ መስሏቸው ሳይጠራጠሩ ቀርተዋል።

ኩባንያው አውቶብሱ መጥፋቱን ያወቀው ከሰዓት በኋላ መደበኛ የሰራተኞች ፍተሻ ካደረገ በኋላ ነው፡፡

ፖሊስ በአውቶብሱ ላይ በተገጠመ የጂፒኤስ መቆጣጠሪያ አማካኝነት ባደረገው ክትትልም፣ ተሽከርካሪው በካርልስሩሄ ከተማ ውስጥ ሊገኝ ችሏል።

ፖሊስ ተሽከርካሪውን ሲያስቆም የ15 ዓመቱን ታዳጊ በሹፌር ወንበር ላይ ያገኘው ሲሆን፣ በወቅቱ የ14 ዓመት ፍቅረኛውን ከትምህርት ቤት ጭኖ ወደ ቤቷ እየመለሳት እንደነበር ታውቋል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ እንደገለጹት ታዳጊው ቁልፉን እንዴት እንዳገኘና ያን ያህል ግዙፍ ተሽከርካሪ ያለምንም እንከን እንዴት ሊነዳ እንደቻለ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ታዳጊውም በአሁኑ ወቅት በስርቆትና ያለ መንጃ ፈቃድ በማሽከርከር ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

በዚህ ያልተለመደ ክስተት ምንም ዓይነት የሰው ሕይወትም ሆነ የንብረት ጉዳት አለመድረሱን እና አውቶብሱም ያለምንም ጉዳት ለባለቤቱ መመለሱን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡

ሐመረ ፍሬው

መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *