የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ “ኮንጎ ኤርዌይስ”ን ለመታደግ የሚያስችል አዲስ ተልዕኮ ጀምረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኘውን የመንግሥት አየር መንገድ ለመታደግ የሚያስችል ስልታዊ ዕቅድ እንዲያወጡ ለጠቅላይ ሚኒስትራቸው ኃላፊነት ሰጥተዋል።
አገራዊው አየር መንገድ የፋይናንስ ችግሮች፣ ከጥገና ጋር የተያያዙ አለመግባባቶች እና ተደጋጋሚ የበረራ መቋረጦች እያጋጠሙት ይገኛል።
በተጨማሪም፤ አየር መንገዱ የነበሩት አውሮፕላኖች በሙሉ በደህንነት ምክንያት ከበረራ እንዲታገዱ በመደረጉ አውሮፕላኖችን በውድ ዋጋ በመከራየት ለአጭር ጊዜ መፍትሔ ለመፈለግ ተገዷል።
ኮንጎ ኤርዌይስ በ2015 ሥራ የጀመረ ቢሆንም፤ ሁለት የኤርባስ አውሮፕላኖች ከሥራ መቆማቸውን፣ ከፍተኛ የጥገና ወጪዎችን እና የደህንነት ችግሮችን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ ችግሮች ገጥመውታል።
በ2021 አየር መንገዱ አራት አዳዲስ አውሮፕላኖችን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል እያቀደ በነበረበት ወቅት፤ ከተጋነነ የክፍያ መጠየቂያ ጋር የተያያዘ የገንዘብ ምዝበራ ክስ ቀርቦበት እንደነበር ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ የቀረበው የአወቃቀር ለውጥ ዕቅድ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ሦስት የኤርባስ አውሮፕላኖችን ለመግዛትና የአስተዳደር መዋቅሩን በድጋሚ ለማደራጀት ያለመ ነው። ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ከመንግሥት በሚገኝ የፋይናንስ ድጋፍ ነው።
በጥር ወር 2025 አዲስ የአመራር ቡድን ቢሾምም የማገገም ሂደቱ ግን ሳይሳለጥ ቆይቷል።
ፕሬዝዳንት ቲሺሴኬዲ የማገገሚያ ስልቱ የአየር መንገዱን አመራር እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል፣ እንዲሁም በሥራ አስፈጻሚዎች መካከል ሥነ-ሥርዓትንና ተጠያቂነትን እንዴት ማስፈን እንደሚቻል በዝርዝር እንዲያሳይ ጠይቀዋል የሚለዉ የአፍሪካ ኒዉስ ዘገባ ነዉ።
ሊዲያ ደሳለኝ
መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
