የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ከምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ህግ ቢሮ ጋር ባደረጉት ኦፕሬሽን ተጠርጣሪዎቹን ካከማቹት በርካታ የኤሌክትሪክ ኬብልና ገመድ ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋል ችለዋል፡፡
ኮተቤ ኪዳነ-ምህረት አካባቢ ተከማችተው የተገኙት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች 4 ሺ 8መቶ95 ሜትር ኤቢሲና ዩጂ የኤሌክትሪክ ኬብሎች፣ 3መቶ50 ኪ.ግ የሚመዝኑ የተለያዩ አልሙኒየምና መዳቦች ሲሆኑ አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 3 ሚሊየን 895 ሺህ 81 ብር ነው፡፡
የተፈፀመው ወንጀል ምስክሮችን በማቅረብ በአፋጣኝ ፍትህ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ተጠርጣሪዎቹ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም የተሠረቁት ኬብሎች በተለያዩ አካባቢዎች አገልግሎት ይሰጡ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ንብረቶቹ ከየት አካባቢ ተዘርፈው እንደመጡ ለማወቅ ምርመራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በተለያየ ጊዜ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ እየተፈፀሙ ያሉት የስርቆት ወንጀሎች ደንበኞችን ለኃይል መቆራረጥ ተቋሙንም ለኪሳራ እየዳረጉ በመሆኑ ህብረተሰቡ ወንጀሉን እንዲከላከል ጥሪ ቀርቧል፡፡
መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
