በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ እና በተለያዩ ግዛቶች ላይ በተሰነዘረ መጠነ ሰፊ የሩሲያ የዘመናዊ ሚሳኤል ጥቃት የ4 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ ወደ 1መቶ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ዋናው የጥቃቱ ኢላማ ዋና ከተማዋ መሆኗን ገልጸው፤ በርካታ የመኖሪያ ህንፃዎች፣ ትምህርት ቤት፣ የኦፔራ አዳራሽ እና ሙዚየም መውደማቸውን አስታውቀዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱን የፈጸመው «ኦሬሽኒክ» የተሰኘውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል በመጠቀም መሆኑን ያመነ ሲሆን፤ እርምጃው ዩክሬን ለሰነዘረችው ጥቃት የተሰጠ ምላሽ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል፣ በሩሲያ ቤልጎሮድ ግዛት በደረሰ የሚሳኤል ጥቃት የሃይል እና የውሃ መሰረተ ልማቶች የተቋረጡ ሲሆን፤ በያሮስላቭ ግዛትም የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ስታሮቢልስክ በተባለች ከተማ በሚገኝ የተማሪዎች መኝታ ክፍል ላይ በሰነዘረችው ጥቃት የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉን ቢገልጹም፣ የዩክሬን ወታደራዊ ክፍል ግን ጥቃቱ ያረፈው በሩሲያ የድሮን የጦር ክፍል ላይ መሆኑን በማንሳት የሲቪል ጥቃቱን አስተባብሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሳራ ዮሐንስ
ግንቦት 17/2018 ዓ.ም
