በቻይና ሸንዘን ዢሊ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በሆነው በዙ ጁንጂ የተመራውና አማካይ ዕድሜያቸው 16 ዓመት የሆኑ ወጣቶችን ያቀፈው ቡድን ይህንን ግዙፍ አውሮፕላን ለመገንባት ስድስት ወራት ፈጅቶበታል።
አውሮፕላኑ የ6.06 ሜትር የክንፍ ስፋትና የ5.06 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ በቅርቡ በተደረገ የሙከራ በረራም በአየር ላይ ለ15 ደቂቃዎች ያህል በተሳካ ሁኔታ መቆየት ችሏል።
የቡድኑ ዋና ዓላማ መሠረታዊ የወረቀት አውሮፕላን መርሆችን ከዘመናዊ ምህንድስና ጋር በማጣመር የተረጋጋና ግዙፍ ሞዴል መፍጠር ነበር።
ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ውድድር ላይ ስኬታማ መሆናቸው ይህንን የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበር መተማመንን የሰጣቸው ሲሆን፣ በአውሮፕላኑ ግዝፈት ምክንያት ያጋጠሟቸውን የክብደትና የንድፍ (ዲዛይን) ፈተናዎችም በብቃት ተወጥተዋል።
ቡድኑ የአውሮፕላኑ ቅርጽ እንዳይዛባ ለማድረግ ቀላል ክብደት ያለውን የ”ኬቲ ቦርድ” ቁስ ከጠንካራው “ካርቦን ፋይበር” ጋር አጣጥሞ መጠቀሙን እና የበረራ አያያዙን ለማቃለልም ንድፉን ደጋግሞ ማሻሻሉ ተነስቷል።
የፕሮጀክቱ መሪ ዙ ጁንጂ ይህ ስኬት የቻይናውያን ወጣቶችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ የፈጠራ አቅም ለዓለም ያሳየ መሆኑን ገልጿል።
ሐመረ ፍሬው
ግንቦት 21/2018 ዓ.ም
