ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ሰልፎች እየተባባሱ መምጣታቸውን እና በከፍተኛ የስራ አጥነት ቁጥር ምክንያት የተፈጠረውን ቅሬታ ተከትሎ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በህገ-ወጥ ስደት ላይ የሚወሰዱ አዳዲስ ጠንካራ እርምጃዎችን ለማሳወቅ ለህዝባቸው ንግግር አድርገዋል።
እርምጃዎቹ፦ ሰነድ የሌላቸውን (ህገ-ወጥ) ሰራተኞች የሚቀጥሩ አሰሪዎችን ማሰር፣ ህገ-ወጥ ስደተኞችን ከሀገር የማስወጣት (ዲፖርቴሽን) ሂደትን የሚያፋጥኑ ልዩ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም እና የማንነት ስርቆትን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት “በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ ሰው” የባዮሜትሪክ መረጃ የያዘ መዝገብ ማዘጋጀትን ያካትታሉ።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ ደቡብ አፍሪካውያን ህግን በገዛ እጃቸው እንዳይወስዱ አስጠንቅቀዋል።
ከፍተኛ ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ከሚል ስጋት የተነሳ፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሀገር ለማስወጣት ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል ሲል ቢቢሲ አፍሪካ ዘግቧል።
የስደተኞች ተቃዋሚ ቡድኖች ህገ-ወጥ ስደተኞች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እየጠየቁ ሲሆን፣ ሰኔ 30 (June 30) የመጨረሻው ቀን እንዲሆን ገድበዋል።
በዚህ ሳምንት መጨረሻም ወደ 140 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በባስ መኪናዎች ወደ ማላዊ እና ሞዛምቢክ ተጉዘዋል።
በደርባን ከተማ ደግሞ የውጭ ሀገር ዜጎች ለህይወታቸው እንደሚሰጉ በመግለጽ፣ ለአንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በከተማዋ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (Home Affairs Department) ደጅ ላይ ድንኳን ጥለው ሰፍረው ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ህገ-ወጥ ስደት በደቡብ አፍሪካ የህዝብ አገልግሎቶች ላይ አላስፈላጊ ጫና እየፈጠረ መሆኑን እና ጉዳዩ በመንግስታቸው መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት አምነዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታትም የሚከተለውን ባለ አምስት ነጥብ ስትራቴጂ አቅርበዋል፦
· የኢሚግሬሽን ህግ ተላላፊዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ
· የድንበር ደህንነትን ማጠናከር
· በኢሚግሬሽን ስርዓት ውስጥ ያለውን ሙስና ማስወገድ
· በኢሚግሬሽን ህጉ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን መዝጋት
· ችግሩን ለመፍታት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ መስራት።
ነገር ግን ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ሲያስጠነቅቁ፦ “የሀገራችንን የኢሚግሬሽን ህግጋት ጨምሮ ሌሎች የህግ ጥሰቶችን መቃወም እና እርምጃ መውሰድ የሚችሉት ስልጣን የተሰጣቸው የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ መሆናቸውን በግልጽ ማሳወቅ እፈልጋለሁ።” ብለዋል።
በመቀጠልም “ማንኛውም ሌላ ሰው፣ ለምሳሌ በመንገድ ላይ ሰዎችን በማስቆም ዜግነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያሳዩ የመጠየቅ መብት የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።
አንዳንድ ተንታኞች እንደሚጠቁሙት በደቡብ አፍሪካ እንደገና ያገረሸው የስደተኞች ተቃውሞ፣ በህዳር ወር ላይ እንዲካሄድ ከታቀደው የአካባቢ ምርጫ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ የተለያዩ ቡድኖች ህዝባዊ የሆኑ ቅሬታዎችን ተጠቅመው ሁከትን በማነሳሳት ሀገሪቱን “ለማናጋት” እንዲንቀሳቀሱ ባለስልጣናቱ እንደማይፈቅዱ ገልጸዋል።
ሰኔ 01/2018 ዓ.ም
