የጣሪያ ፀሐይ ኃይል ልማት ብሔራዊ መመሪያ የተሰኘዉ ይህ መመሪያ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ተነግሯል።
መመሪያዉን ያዘጋጀዉ የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሲሆን፤በቤትና ሕንፃ ጣሪያ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ እንዲሚገጠም የሚያስቀምጥ መመሪያ መሆኑን ተገልጿል።
በዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ሀብት ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚዉ አቶ ካሌብ ታደሰ ፤ የመመሪያዉ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ መሆኑ እና ከሰኔ 30 በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል።
አቶ ካሌብ እንደገለፁት፤ ሀገሪቱ ከፍተኛ የፀሀይ ሀይል አቅም ያላት መሆኑን ተከትሎ ይህ መመሪያ ይህንን የኢነርጂ አቅም ለመጠቀም እንዲቻል ያለመ ነዉ ብለዋል።
የጣሪያ የፀሐይ ኃይል ልማት እና አጠቃቀም መመሪያ ዜጎች በቤት እና በህንፃ ጣሪያ ላይ ይህን ቴክኖሎጂ ገጥመዉ እንዲጠቀሙ መመሪያዉ አስገዳጅ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዚህ የመመሪያ ዝግጅት ላይ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ ተቋማት እና ባለሙያዎች ጋር ዉይይት አድርጌበታለሁ ብሏል።
ታሪፍ የሚያወጣዉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ህንፃ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጋር ከዚህ በኋላ የሚገነቡ ህንፃዎች ጣሪያ ለዚህ ቴክኖሎጂ እንዲያመች ሆኖ እንዲዘጋጅ ዉይይት መደረጉን አቶ ካሌብ ተናግረዋል።
የዚህ ቴክኖሎጂ ትግበራን በመጀመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የማድረግ እቅድ መኖሩን ተከትሎ፤በአዲስአበባ የዚህ ቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም በእያንዳንዱ ጣሪያ ላይ ምን ያህል ሀይል ማግኘት እንደሚቻል የጠየቅናቸዉ አቶ ካሌብ፤በተቋም ደረጃ ይሄን የሚመልስ ጥናት ማድረግ እንዳልተቻለ ሆኖም ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂዉን የመግዛት አቅም እንደመጀመሪያው የሚፈትን መሆን እንደ ስጋት የተቀመጠ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ካሌብ ፤ ለዚህ እንደመፍትሄ ህብረተሰቡ ይህንን እንዲጠቀም ማበረታቻዎች መቀመጥ እንዳለባቸዉ የስትራቴጂ አቅጣጫዎች አሉ ብለዋል።
ቁምነገር አየለ
ሰኔ 01/2018 ዓ.ም
