የታክስ ማጭበርበር ምርመራን ወደ ኋላ 10 ዓመት መመለሱና የመሠረተ ልማት እጥረቶች በነጋዴው ላይ ያሳደሩት ስጋት በፓርላማው ውይይት ተነስቷል፡፡
በትላንትናው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ላይ፣ የታክስ ማጭበርበር ወንጀልን ወደ ኋላ 10 ዓመት ተመልሶ እንዲመረመር የሚያዝዘው ድንጋጌ፣ ከፍ ያለ የቅጣት ተመን እና የኔትወርክ መሠረተ ልማት ችግሮች በታክስ ከፋዩ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ስጋትና እንቅፋት መፍጠራቸው ተገልጾ ለውይይት ቀረበ።
በተለይም በታክስ ማጭበርበር የተጠረጠረ አካልን እስከ 10 ዓመታት ወደ ኋላ ሄዶ ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑ በውይይቱ ተሳታፊዎች በስፋት የተተቸ ሲሆን፣ የንግድ ማህበረሰቡ ሀሰተኛ ደረሰኞችን የሚያረጋግጥበት ቴክኖሎጂ በሌለበት ሁኔታ የተጋነነ ቅጣት መጣሉ አግባብ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።
ከዚህም በተጨማሪ የታክስ ጉዳዮች በድርድር እንዲፈቱ መደረጉ ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍት መሆኑ፣ ከግብር ተመን ጋር የተያያዙ ከፍተኛ ችግሮች መኖራቸው እንዲሁም የኔትወርክ መሠረተ ልማት መቆራረጥ ለታክስ ከፋዩ ዋነኛ ማነቆ መሆናቸውን በመጥቀስ ተሳታፊዎቹ ጠንካራ ቅሬታና ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ታክስ አስቀድመው ያላሳወቁ ድርጅቶችም ምክንያታቸው በአግባቡ ሳይጣራ በቀጥታ ወደ ቅጣት መግባት እንደሌለባቸውና የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜም ሊታይ እንደሚገባ ተገልጿል።
ለተነሱት ስጋቶች ምላሽ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፣ የታክስ ማጭበርበርን ጉዳይ ወደ ኋላ 10 ዓመት ተመልሶ እንዲታይ የተደረገበት ምክንያት በቀደመው አዋጅ ላይ ምንም ዓይነት የጊዜ ገደብ ባለመቀመጡ እንደሆነ አብራርተዋል። ይህ አዲስ ድንጋጌ እንዲያውም የተወሰነ የጊዜ ገደብ ለማስቀመጥ በማለም የገባ መሆኑን ጠቁመው፣ ከደረሰኝ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችም በቀጣይ አሠራሮችን በማዘመን እንደሚፈቱ አስታውቀዋል።
ከትላንትናው የሕዝብ ውይይት ጎን ለጎን፣ ይኸው የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አብዛኛዎቹ ድንጋጌዎቹ የተቋሙን አገልግሎት በእጅጉ የሚያቀላጥፉና ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ የግብር ከፋዩን ችግሮች የሚፈቱ መሆናቸው ተገልጿል።
የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሃብረቢ እንደገለጹት፣ አዋጁ ላለፉት አስር ዓመታት ያገለገለ በመሆኑና ሀገሪቱ ካደረገቻቸው በርካታ ሪፎርሞች ጋር አብሮ የሚሄድ ሙሉ ማሻሻያ የሚፈልግ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ያጋጠሙ አንገብጋቢ ችግሮችን ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት ሲባል አዋጁ እንዲሻሻል መደረጉን አስረድተዋል።
ዘገባውን ስናዘጋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽን እና የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ተጠቅመናል ።
ለዓለም አሰፋ
ሰኔ 09/2018 ዓ.ም
