ሶማሊላንድ ህጋዊ ሰነድ የሌላችሁ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሬን ለቃችሁ ዉጡ ስትል አሳሰበች

የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ህገወጥ የውጭ ሀገር ዜጎች በ10 ቀን ውስጥ ሀገሪቱን ለቃችሁ ውጡ ማለታቸው ተዘግቧል።

ባለስልጣናቱ ይህን ያልነው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን የማስፈን ስራን ለማጠናከር ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ሚንስትር የሆኑት አብዱረሺድ ሙሀመድ አህመድ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ የደህንነት አካላት አዋጁን በጥንቃቄ እንድናስፈፅም ትዕዛዝ ሰጥተውናል ነዉ ያሉት፡፡

አክለውም ‹‹የደህንነት አካላት ዜጎቹ በአስር ቀን ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው መውጣታቸውን ለማረጋገጥ ይሰራሉ፣ ህዝባችንም የሚጠረጥረውን ማንኛውንም ሰው ለደህንነት አካላት የመጠቆም ሀላፊነት አለበት›› ብለዋል።

ሚኒስትሩ ሀገራችን አለም አቀፍ ትኩረት እየሳበች በመሆኑ ወደፊት የኢንቨስትመንት ስራዎችንና የስራ ዕድሎችን ስለምንጠብቅ አሁን ላይ ደህንነታችን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ማለታቸውን ሂራን ዘግቧል።

ዘገባው አያይዞም ማህበረሰቡ ህግን የማስከበር ጉዳይ ውስጥ መግባት የለበትም፤ከውጭ ዜጎች ጋር ተያይዞ ከጥቆማ የዘለለ ምንም አይነት እርምጃ እንዳይወስዱ አስጠንቅቀዋል ሲል አስነብቧል።

ሆኖም አዋጁ ህጋዊ የሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎችን ባያካትትም ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በስደተኞች ጉዳይ ማስጠንቀቂያዎችን መስጠቷ የሚታወስ ነው።

ለውጭ ሀገር ዜጎች ለስራ እንዲሁም የመኖርያ ቪዛ የምትፈቅደው ሀገሪቱ ከህግ ውጪ የሆኑ ሰዎች የሀገሪቱን የስደተኞችን ህግ እንዲያከብሩና ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች።

ሃናን ሸምሱ

ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *