የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ ተካሂዶ ስለነበረው ሀገራዊ ምርጫና በሂደቱ የታዩ ተግዳሮቶችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ምርጫው የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ጉዞ ለማደናቀፍ በሚፈልጉ አካላት ዘንድ ቀጥተኛ የጥቃት ኢላማ ሆኖ እንደነበር ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ከነበረበት የፖለቲካ ፉክክር ባለፈ፣ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ውሳኔ የመፈተን ሂደት እንደነበር አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የዘንድሮው ምርጫ በተለመደው የፖለቲካ ውድድር ብቻ የታጠረ አልነበረም።
ይልቁንም ምርጫው ራሱ እንደ አንድ የጥቃት ኢላማ ተወስዶ፣ እንዳይካሄድና ከተካሄደም የግርግር መነሻ እንዲሆን በውስጥና በውጭ ኃይሎች ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት ቆይቷል።
“ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች በተለየ መልኩ፣ የዘንድሮው ምርጫ በከፍተኛ የጥፋት ሴራዎችና ዛቻዎች ተከቦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህን ሁሉ አልፎ በስኬት ተጠናቋል” ብለዋል።
በምርጫው ሂደት ላይ ሲሰነዘሩ የነበሩ አሉታዊ ግምቶችን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ምርጫውን ማድረግ አትችሉም፣ ኢትዮጵያ ትበታተናለች” የሚሉ ድምፆች በስፋት ይሰሙ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ምርጫውን በሰላም ማካሄድ መቻሉ እነዚህን የጥርጣሬ ደመናዎች የገፈፈና “ማሸነፍ ማለት ከፈተና መሻገር ነው” የሚለውን እውነት በተግባር ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ስኬት ለሀገሪቱ የፖለቲካ ብስለት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም አክለዋል።
መራጮች በቤታቸው ካለው ሐዘንና ካለባቸው የእድሜ ጫና በላይ የሀገር ጉዳይ በልጦባቸው፣ ወጥተው ድምፅ መስጠታቸው ትልቅ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የጥፋት ኃይሎች ጥይት እየተኮሱ ሕዝቡን ለማስፈራራት ቢሞክሩም፣ ዜጎች ግን ለአፍታም ሳይሸበሩ ረጅም ሰልፎችን ይዘው መመረጣቸው “ጥልቅ ስኬት” እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ የከፈለውን መስዋዕትነትና ያሳየውን ጽናት “ትልቅ አደራ” ሲሉ ጠርተውታል። “በዚያ ሁሉ መከራና ስጋት ውስጥ ወጥቶ የመረጠን ሕዝብ የሰጠን ድምፅ ዝም ብሎ ወንበር ሳይሆን፣ ከባድ አደራ ነው” ብለዋል።
መንግስትም ይህንን የሕዝብ አደራ ተረድቶ፣ የዜጎችን ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
ለዓለም አሰፋ
ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
