በትግራይ ከሚኖሩት ይልቅ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ የትግራይ ተወላጆች የተሻለ የሰላም ዕድል እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለጹ፤ ከ60 ሺህ በላይ ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታታቸውም ተናግረዋል

በትግራይ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት ይልቅ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የተሻለ የሰላምና የመንቀሳቀስ ዕድል እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ መንግሥት ዳግመኛ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌለውና ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈጻሚነት እየሠራ መሆኑን አስታወቁ።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ እስካሁን ከ60 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች በዲዲአር (DDR) መርሃ ግብር አማካኝነት ትጥቅ መፍታታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ መንግሥት ዳግመኛ ወደ ግጭትና ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር፤ በትግራይ ክልል ውስጥ ባለው አለመረጋጋት በርካታ የትግራይ ልጆች በጉልበት ታፍሰው እስከ ሱዳን መሸጣቸውን በመጥቀስ ሕዝቡ አሁንም ድረስ በሰላም እጦት ምክንያት መከራ እየደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል።

የዜጎችን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ያነጻጸሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በትግራይ ውስጥ ከሚኖር ትግራዋይ በተሻለ በሌላ የሃገሪቱ ክፍል ያለ የትግራይ ልጆች በሰላም ወጥተው ይገባሉ” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በደሴ፣ በጎንደር፣ በአዳማና በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የተሻለ የመንቀሳቀስ ዕድልና ደህንነት እንዳላቸው በመጥቀስ፤ ይህ ሁኔታ ለአማራ እና ለኦሮሞ ልጆችም ጭምር ተመሳሳይ መሆኑንና ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነፃነት የመኖር መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግሥት ዘላቂ መረጋጋትን በመፍጠር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ዐቢይ፤ በሰላም ስምምነቱ መሠረት ምርኮኞችን የመፍታት እርምጃ መወሰዱንና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለሕዝብ ክፍት እንዲሆኑ መደረጉን በስኬትነቱ አንስተዋል።

በሌላ በኩል ሰላምን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን በጽኑ የኮነኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የሰላም አደናቃፊዎቹ ቤተሰቦች አንዳንዱ በአዲስ አበባ፣ አንዳንዱ ደግሞ በውጭ ሀገራት ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩና እየኖሩ፣ የትግራይን ሕዝብ ግን ለሰላም እጦት ይዳርጋሉ” ሲሉ ወቅሰዋል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሰጠ ቢሆንም፣ አሁንም ባለው አለመረጋጋትና የጥፋት ኃይሎች እንቅስቃሴ ምክንያት የችግሩ ገፈት ቀማሽና ዋነኛ ተጎጂ የትግራይ ሕዝብ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ለዓለም አሰፋ

ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *