ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀስላሴ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በይፋ አስጀመሩ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀስላሴ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተመሠረተበትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓልና አውደ ርዕይ በዛሬው ዕለት በይፋ ከፍተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ተቋሙ ባለፉት መቶ ዓመታት የዜጎችን ጤና ለመጠበቅና ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ያደረገው ጉዞ የኢትዮጵያ ብርቱ ትግል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በወጣትነት ዘመናቸው ተቋሙ “ፓስተር” ተብሎ በሚጠራበት ወቅት የነበረውን ትውስታ በማውሳት፣ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የባለሙያዎች መስዋዕትነት ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

“ይህ 100 ዓመት ቀላል አይደለም፤ በሂደቱ የታየው የባለሙያዎች ቁርጠኝነትና ታሪክ ጎልቶ ሊጻፍ ይገባል” ብለዋል።

የሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደኅንነት ከዜጎች ጤና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የገለጹት ፕሬዝዳንት ታየ፣ ኢንስቲትዩቱ እንደ ኮቪድ-19፣ ኤም-ፖክስና ማርበርግ ያሉ ወረርሽኞችን በመመከት ረገድ ያሳየው ሳይንሳዊ አመራር የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተቋሙ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ይበልጥ በማጠናከር ለቀጣዩ መቶ ዓመት ራሱን እንዲያዘጋጅም ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስዓለም አበበ

ሐምሌ 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *